የሲዳማ የባህልና ቋንቋ ሲምፖዚየም ተካሄደ

80
ሀዋሳ ነሃሴ 10/2010 በሃገር ደረጃ እየታየ ያለው ለውጥ ህዝቡ አንድነቱን ጠብቆ በሁሉም መስክ  ተጠቃሚነቱን እንዲያረጋግጥ የሚያግዝ መሆኑን የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ገለጹ፡፡ 24ኛው የሲዳማ ብሄር የባህልና ቋንቋ ሲምፖዚየም ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተካሄዷል፡፡ በዚህ ወቅት  ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት ሲምፖዚየሙ ሃገሪቱ በለውጥ ሂደት ውስጥ ባለችበት ወቅት የተካሄደ  በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል፤ለውጡ የሲዳማ ብሄር አንድነቱን ጠብቆ በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚነቱ እንዲያረጋግጥ የሚያግዝ ነው፡፡ የመጣው ለውጥ ውጤታማ እንዲሆን አመራሩ ፣ምሁራን፣ወጣቶችና የሃገር ሽማግሌዎች ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ የአሁኑ ትውልድ በአዲስ አመለካከትና አስተሳሰብ ጥያቄውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማራመድ እንደሚጠበቅበት ጠቅሰው የለውጥ እንቅስቃሴው ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስዱ የሚፈልጉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል፡፡ ለውጥ ህብረተሰብን እንጂ አለአግባብ የጥቂቶች መጠቀሚያ እንዳይሆን መጠንቀቅ እንደሚገባ ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ " የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች በአንድነት መፍታት ያስፈልጋል "ብለዋል፡፡ የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቃሬ ጫዊቻ በበኩላቸው ሲምፖዚየሙ ባለፉት 24 ዓመታት  ሲከበር ለብሄሩ ባህልና ቋንቋ እድገት ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ ያልተከናወኑ በርካታ ተግባራት በመኖራቸው ችግሮቹን ለይቶ በዘርፉ ከሚሰሩ ምሁራንና ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ " ቋንቋውን ለስነ ጽሁፍ ከማዋልና በስራ አካባቢዎች በሚፈገለው ልክ አለመጠቀም በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ናቸው "ያሉት ደግሞ የዞኑ ባህል ቱሪዝምና መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ጃጎ አገኘሁ ናቸው፡፡ ቅርሶችን በመንከባከብና በማልማት ረገድ ውስንነቶች አሉ ብለዋል፡፡ በቋንቋ ረገድ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ በመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት መሰጠቱ፣ መዝገበ ቃላትን ጨምሮ የተለያዩ መጽህፍት መታተማቸው ባለፉት ዓመታት የተገኙ ድሎች እንደሆኑም አውስተዋል፡፡ በባህል ረገድም የፊቼ ጨምባላላ በዓል የአለም ቅርስ መሆኑ ሌላው ስኬት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ የሲምፖዚየሙ ተሳታፊ የነበሩት የባህል ጥናትና ምርምር ባለሙያው አቶ ብዙአየሁ ላቀው ፡ህገ መንግስቱ ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህልና ቋንቋ እድገት የሰጠው እድል ማንነታቸው እንዲታወቅና  በአፍ መፍቻቸው እንዲናገሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ "ባህል በውስጡ በርካታ እሴቶችን መያዙ እየታወቀ በመንግስት ደረጃ በቂ በጀት አለመመደቡ የዘርፉ ውስንነት ነው "ብለዋል፡፡ በሲምፖዚየሙ የሲዳማ ባህላዊ አስተዳደርና በስም አወጣጥ ላይ ያተኮሩ  የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ የብሄሩን ታሪክና ባህል የሚያሳዩ ቅርሶችም ለህዝብ እይታ በቀረቡበት ሲምፖዚየም የብሄሩ ተወላጅ ምሁራንና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም