መልኩን የቀየረው የምዕራባዊያን ጫና “በቃን”

150

አንድ አገር የሰብዓዊ ድጋፍ የሚሰጡ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ግለሰቦችን “ተጠያቂ ሆነው አግኝቻለሁ፤ ከተስማማንበት ዓላማ ውጭ ሰርተዋል” በሚል ከአገሩ ማባረር አይችልም? “ጠላቴን እየደገፈ፣ አቅሙን እያበረታና የእኔን ሰላም እየነሳ ሊኖር አይገባውም” በማለት ውሳኔ ሲሰጥ “አንተ ማነህ?” እንዴት ይባላል? የሚል ጥያቄ ማቅረባችን አይቀርም።

በአሜሪካ የፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር ባለስልጣናት ግልጽ በሆነ መንገድ ለአሸባሪው ሕወሃት ሲያደሉ ተስተውሏል። የአሸባሪውን ህወሃት ወንጀል ሰምተው እንዳልሰሙ፣ አይተው እንዳላዩ ሆነው አልፈዋል። ይልቁኑ በሀሰት ቅንብር የተሰራ የምርመራ ዘገባ በሚል ተጨባጭነት የሌለው ትርክት ተቀብለው ሲያስተጋቡና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር ሲሞክሩ ትዝብት ላይ ወድቀዋል። የጥርስ ሀኪሙ የፎረንሲክ ተመራማሪ ሆኖ የሌለ ውጤት ሲያወራ “ልክ ነው” በሚል ማጨብጨባቸውን አስተውለናል።

የፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር ተግባር ባይደንቅም አገራችን ከአገሮች ጋር በመተባበር የመሰረተችውና “በክፉ ወቅት ይታደገናል” ብላ ያመነችበት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ)፤ መንግስት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል ያላቸውን ሰባት የመንግስታቱ ድርጅት ሰራተኞች በ72 ሰዓት አገሪቷን ለቀው እንዲወጡ ማዘዙን ሲሰማ ስለጉዳዩ ማብራሪያ ከመጠየቅና መረጃ እፈልጋለሁ ከማለት ይልቅ ሰራተኞቼ “ስህተት የማይሰሩ የምንተማመንባቸው ናቸው፤ በኢትዮጵያ መንግስት እርምጃ ደንግጫለሁ” በማለት በድንጋጤ ውስጥ ሆነው “እርምጃው ይቀልበስ” የሚል ጥያቄ ሲያመጣ ድርጅቱ ለአንድ ወገን የሚያጨበጭብና የሚሰራ መሆኑን አሳይቷል።

መንግስት ለዚህ ዓይነቱ ትዕዛዝና ውሳኔ የደረሰው በሰብዓዊ ድጋፍ አመካኝተው በአገር የውስጥ ጉዳይ ገብተው ሲፈተፍቱ በመገኘታቸው መሆኑን ይፋ አድርጓል። “አንዳንዶች ለሕክምና ሥራና ለጤና አገልግሎት መጥተው፣ ጤናን በሚያዛቡና የኅብረተሰቡን ሰላም በሚያደፈርሱ ተግባራት ላይ ይሰማራሉ፡፡ ለውሃ ቁፋሮ ይመጡና አገር ሲቆፍሩ ይታያሉ፡፡ ይህ ዓይነት ተግባር ደግሞ በየትኛውም አገር አይፈቀድም» ሲሉ በአገር ውስጥ ጉዳይ ምን ያህል እየፈተፈቱ መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የተናገሩትን እዚህ ላይ መጠቀስ ይቻላል።

የኢትዮጵያ መንግስት የተመድ ባለሙያዎች ካደረጓቸው ህገ ወጥና ኢ - ሥነ ምግባራዊ ተግባራት መካከል፤ 

  1. ለተቸገረውና ዕርዳታ ለሚያስፈልገው ህዝብ ተብሎ የመጣን የሰብዓዊ ድጋፍና ዕርዳታ ለአሸባሪው ህወሃት አሳልፎ መስጠታቸው፣
  2. ከመንግስት ጋር የተደረገን ስምምነት መጣሳቸው
  3. የተለያዩ የመገናኛ መሳሪያዎችን አሸባሪው ህወሃት እንዲጠቀምበት ማስተላለፋቸው፣
  4. ለሰብዓዊ ደጋፍ የሚውሉ ቁሳቁሶችን ይዘው ወደ ትግራይ የገቡና ሳይመለሱ የቀሩ ተሽከርካሪዎች በአሸባሪው ህወሃት ቁጥጥር ስር መሆናቸውና ለወታደራዊ ተግባር መዋላቸውን እያወቁ እንዲመለሱላቸው ለመጠየቅ ቸልተኝነት ማሳየታቸው እና 
  5. ሀሰተኛና የተዛቡ መረጃዎችን ማሰራጨታቸውና ሰብዓዊ ድጋፍን ለፖለቲካ ዓላማ እንዲውል ማድረጋቸው የሚጠቀሱ ናቸው።

እነዚህ ከኢ ₋ ስነ ምግባራዊ ጉዳዮች የዘለሉና የአገርን ሉዓላዊነትን የሚዳፈሩ ናቸው። የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ሕወሃትንና ሸኔን” አሸባሪ በማለት ፈርጇል። ይህን ያደረገው ለዜጎች በሰላም መኖር ጠንቅ፣ ለአገር አንድነትና እድገት አደገኛ አካሄድ እየተከተሉ መሆኑን በማመን የወሰደው እርምጃ ነው። 

መንግስት በዓለምአቀፉ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩና ከዓላማቸው ውጪ የኢትዮጵያን ጥቅም በሚጎዳ ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ ሰባቱ የውጭ ዜግነት ያላቸው የተመድ ሰራተኞች ላይ የተወሰደው እርምጃ ሕጋዊነትን ለማስፈን የተወሰነ መሆኑን ይፋ ተደርጓል።

እነዚህ ሰራተኞች በኢትዮጵያ ምድር ለ72 ሰዓት እንዲቆዩ መደረጉ አሜሪካን ክፉኛ “አስጨንቋታል”። የአሜሪካ መንግስትና ባለስልጣናቱ “በጥብቅ አወግዛለሁ፤ እርምጃም ለመውሰድ ወደ ኋላ አንልም” በማለት ሲያሳውቅ፤ የተመድ ዋና ጸሀፊ ጉተሬዝ ደግሞ “እርምጃው እንዲቀየር ከመንግስት ጋር እነጋገራለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል። የባይደን አስተዳደር ባለስልጣናት የዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ጉዳይ ያስጨነቃቸው አይመስልም። ዲፕሎማሲ ገደል ይግባ በሚል ሰዎቹን ወደ ስራ ባትመልሱ “ . . . this decision to be reversed and will not hesitate to respond decisively.” በማለት የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሃላፊ አንቶኒዮ ብሊንከን የገለጹት ሀሳብ ዲፐሎማሲያዊ ያልሆነ፣ የበላይነት ስሜት የተጠናወተው፣ በሌላ አገር “ጣልቃ መግባት መብታችን ነው” የሚል መልዕክት አዝሏል። ኢትዮጵያ ግለሰቦቹን በማባረሯ ይሄን ያህል ያስቆጣት፤ ተቋማቱ ቢዘጉ ምን ልትል ነው? ሠራዊቷን ልታዘምት ነው? የዓለም ሚዛን ማጣት ጥሩ ማሳያ ነው። 

በርግጥ እርምጃውን መንግስት ካሳወቀ በኋላ የተለያዩ አገሮች የሰጡት ምላሽ የኢትዮጵያን ምክንያት ከመስማትና ሚዛናዊ ውሳኔ ከመስጠት ይልቅ “በፍጥነት እንድትመልስ የሚያዝ ነው”።

የተመድ ሰራተኞች ጉዳይ ለአሜሪካ የእግር እሳት ሆኖባት “ቅጣቴን አጠነክራለሁ” በማለት በቃል አቀባይዋ በኩልም አስታውቃለች። ለዚህም እንደምክንያት የቀረበው የሰብዓዊ ድጋፍ አድራጊ ተቋም ሰራተኞች መሆናቸው ነው።  

ቁም ነገሩ የባይደን አሰተዳደርና የዓለም አቀፍ ተቋማቱ ለሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ወይስ ኢትዮጵያን እጅ ጠምዝዞ የራስን ፍላጎት ለመጫን? የሚለው ምላሽ ማግኘት አለበት።

የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ አድርጎ ከትግራይ ክልል ከወጣ በኋላ አሸባሪው ህወሃት በአፋርና በአማራ ክልሎች በመስፋፋት ከ600 ሺህ በላይ ዜጎችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሎ ችግር ውስጥ ሲከት የትኛውም አገር ለማውገዝ አልሞከረም።

በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በአሸባሪው ህወሃትና በአምሳያው ሸኔ በርካታ ንጹሀን ሲገደሉ፣ በጅምላ ሲጨፈጨፉና አካለ ጎዶሎ ሲሆኑ ድምጻቸውን አላሰሙም። ከሰው አልፎ እንስሳት ገድሎ ሲፎክርና ለዜጎች የቀረበ ምግብና ምግብ ነክ እርዳታዎች ሲዘርፍ አሸባሪውን ማንም “በቃህ” አላለም።

የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የአፋርና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ሕዝቦች ህይወት ለባይደን አስተዳደርና ለምዕራባዊያን አይገዳቸውም። የእነርሱ መራብ፣ መጠማትና መሞት፣ በክረምት ከቤት ንብረታቸው መፈናቀል አልተሰማቸውም። በዝምታቸውና በእጅ አዙር አሸባሪን እየደገፉ፤ በተግባር ግን የኢትዮጵያን መንግስት በሰብዓዊ እርዳታ ሰበብ ይኮንናሉ።     

ማይካድራ ላይ ዜጎች በዘራቸው ብቻ ተለይተው መጨፍጨፋቸው እውነት መሆኑን እየጎፈነናቸውም እውነትነቱን ቢቀበሉም አንድም የቁጣ ድምጽ አላሰሙም። አፋር ላይ የደረሰው ጭፍጨፋ አላመማቸውም። በረሃብ ሰቆቃ እየወደቁ ያሉት የአማራ ክልል ሰዎች ሰቆቃ አልከነከናቸውም። 

ኢትዮጵያ ግን ለእነዚህ ዜጎቿ ታስባለች፤ በአሸባሪው ህወሃት የስልጣን ጥምና ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርሳቸው ታግተው የመከራ ስቃይ የሚበሉና ሰብዓዊ ጋሻ የሆኑ የትግራይ ህዝብ ስቃይና ለምግብ እጥረት መጋለጥ ያሳስባታል። 

ይህ ስለሆነም እርዳታ በቦታው እንዲደርስ የምትችለውን መንገድ ሁሉ ከፍታለች። ከ450 በላይ የእርዳታ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ህግን በጠበቀ መልኩ ወደ ትግራይ እንዲገቡ ተደርጓል። ከ400 በላይ ተሽከርካሪዎች አልተመለሱም። አሸባሪው ህወሃት ‘ምን ታመጣላችሁ? ታጣቂዎቼን አመላልስበታለሁ’ ሲል በይፋ ያለምንም መሸማቀቅ ሲናገር እዚህ ያሉት እንኳን “እንዴት?” ከማለት ይልቅ መንግስትን ለማሳጣት ይሞክራሉ።

የዚህ ዓይነቱ ድርጊት ህገ ወጥነት፣ ሉዓላዊነትን መዳፈር ነው። በጫና የሚመጣ ሰላም እንደሌለ፣ የሚመጣ ሀሳብን የማስረጽ አቅም እንደማይፈጠር ለ20 ዓመታት ዜጎቿን በአፍጋኒስታን ስታንከራተትና ስቃይ ስታበላ ከቆየችው ከራሷ ከአሜሪካ በላይ ምስክር የለም። በደንብ ታውቀዋለች። ሕዝብን ከራሱ ባህል፣ እሴትና ማንነት ውጪ በሃይልና የውጭ ፍላጎትን የራስን አስተሳሰብ ለመጫንና ጥቅምን ለማስጠበቅ ዋጋ ከመከፈል ባሻገር ውጤታማ ያለመሆኑን ሊቢያ፣ ሶሪያ፣ የመን፣ ሶማሊያና አፍጋኒስታን ምስክር ናቸው።

ለአሜሪካ ንፁሃንን ገድሎ ይቅርታ መጠየቅ፣ አገር አፍርሶ “የተሳሳተ ወሳኔ ነበር” ማለት ባይከብዳትም የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ በተለየም አፍሪካውያን ጠንቅቀው መረዳት ያለባቸው ዓለም “በአንድ ሃያል የምትሽከረከርበት ዘመን በቃ” የማለት አቅምን መፈጠር፤ በጋራ መታገልን ነው። 

“በቃ” የምንለው ደግሞ አፍሪካውያን በህብረት ስንታገል፣ ስንወድቅና ብዙዎችን ስናፈራ ነው። ኢትዮጵያውያን አያቶቻችን ትናንት “አይቻልም” ብለው የተከበረ አገር አስረክበዋል፤ ዛሬም “እጅ መጠምዘዝ በቃ፤ በእርዳታ ስም ማስፈራራት ይገታ” በማለት ድመጿን እያሰማች ነው። አፍሪካውያን ሊከተሏት ይችላሉ። ለነገ ደግሞ አፍሪካውያን በራሳቸው የብልጽግና መንገድ ታላቅ ማማ ላይ ለመወጣት እንደሚችሉ እያወጀች ነው።        

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም