በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 177 የህግ ታራሚዎች በይቅርታ ተፈቱ

85
አሶሳ ነሃሴ 10/2010 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 177 የህግ ታራሚዎች በይቅርታ መፈታታቸውን የክልሉ ፍትህ ቢሮ አስታወቀ፡፡ በቢሮው የይቅርታ ቦርድ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ንጋቱ ዓለሙ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ዛሬ የተደረገው ይቅርታ የክልሉ የይቅርታ ቦርድ በአመት አራት ጊዜ አገልግሎቱን ለመስጠት በሚያዘው መሠረት የተፈጸመ ነው፡፡ በይቅርታ ከተፈቱት መካከል ዘጠኙ ሴቶች ናቸው፡፡ ''ይቅርታውን ያገኙት በፈፀሙት ወንጀል እስከ እድሜ ልክ የተፈረደባቸው ታራሚዎች ይገኙበታል'' ብለዋል፡፡ በይቅርታ የተፈቱት ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ከፈጸሙት ወንጀል ተጸጽተው መታረማቸው በመረጋጡ በክልሉ ይቅርታ ቦርድ እንዲፈቱ መወሰኑን ጠቅሰዋል፡፡ እርሳቸው እንዳሉት ይቅርታው የግድያና መሠል ወንጀሎችን የፈጸሙትን አይመለከትም፡፡ ይቅርታ ከተደረገላቸው መካከል አቶ አምቢሳ ያደታ “ሰርቶ መኖርና መለወጥ ሲቻል ወንጀል ሰርቶ ወደ ማረሚያ መውረድ አስከፊ ነው” ብለዋል፡፡ ወንጀል ራስን፣ ወገንንና ሀገርን የሚጎዳ በመሆኑ ሌሎች ከድርጊቱ እንዲቆጠቡ ለማስተማር መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም