በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር በክረምቱ የተተከሉ የዛፍ ችግኞች እንክብካቤ እየተደረገላቸው ነው

65
ባህርዳር  ነሃሴ 10/2010 በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በተያዘው የክረምት ወቅት በህብረተሰቡ ተሳትፎ  የተተከሉ የዛፍ ችግኞችን  ከአረም በመከላከልና በመኮትኮት እንክብካቤ እየደረገላቸው መሆኑ ተገለጸ፡፡ በዞኑ ግብርና መምሪያ የስነ-ህይወታዊ ጥበቃና ጥምር ደን ባለሙያ አቶ አዲሱ ስማቸው እንደገለጹት በክረምት ወቅት  ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ከ104 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል። ባህርዛፍና ፅድን ጨምሮ የተተከሉት  የተለያዩ የዛፍ ችግኞች  በበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ በተሰራባቸው፣ ለምነቱን ባጣና በተራቆተ ዘጠኝ ሺህ 400 ሄክታር የወልና የግል መሬት ላይ ነው። የችግኞቹ ልማት  36 በመቶ ላይ የሚገኘውን የዞኑን የደን ሽፋን ወደ 37 በመቶ እንደሚያሳድገው ይጠበቃል። ህብረተሰቡም በክረምት ወቅት በግልና በጋራ የተከላቸውን ችግኞች ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ እንዲጠበቅ ከማድረግ ባለፈ የአረምና ኩትኳቶ ስራ እያካሄደ መንከባከቡን እንደቀጠለ  ባለሙያው ተናግረዋል። በተለይ በ2001 ዓ.ም. በተጠናከረ መልኩ የችግኝ ተከላ ከተጀመረ ወዲህ የዞኑ የሰው ሰራሽ ደን ሽፋን ከ23 ሺህ ሄክታር ወደ101 ሺህ 214 ሄክታር ማደጉንም ጠቁመዋል። የሰው ሰራሽ ደን ሽፋኑ በፍጥነት እያደገ የመጣው አርሶአደሩ በደን ውጤቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን በየጊዜው እያረጋገጠ በመምጣቱ ነው። ባለፈው ዓመት ከተተከለው 122 ሚሊዮን ችግኝ ህብረተሰቡ ባደረገው እንክብካቤ 82 በመቶ ፀድቆ በጥሩ የእድገት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ባለሙያው አመልክተዋል። በዞኑ ባንጃ ወረዳ የከሳቸውሳ ቀበሌ ነዋሪ ቄስ ታረቀኝ ቦጋለ ለኢዜአ እንዳሉት  ለምነቱን ባጣ ሩብ ሄክታር የግል መሬታቸው በክረምት ወቅት የተከሉትን ሁለት ሺህ 600 የዛፍ  ችግኝ እየተንከባከቡ ነው፡፡ ከሶስት ዓመት በፊት ምርት መስጠት አቁሞ በነበረ አንድ ሄክታር መሬት ተክለው ካለሙት ሰው ሰራሽ ደን  ሽያጭ 50 ሺህ ብር ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ ሆነዋል። ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋርም በተፋሰሶቹና በወል መሬቶች በጋራ የተከሉትን ችግኝ የአረምና ኩትኳቶ ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ። ሰብል ማምረት ያቆመ አንድ ሄክታር ተኩል መሬታቸውን በደን ዛፍ ማልማታቸውን የገለጹት ደግሞ  በፋግታ ለኩማ ወረዳ የአዝማች ጉላ ቀበሌ ነዋሪ ቄስ አንዱዓለም ተስፌ ናቸው፡፡ ካለሙት ደንም ለምርት የደረሰውን ባለፈው ዓመትና ዘንድሮ በመሸጥ ከ66 ሺህ ብር በላይ ገቢ አግኝተዋል። ቄስ አንዱዓለም እንዳስረዱት ቆርጠው በሸጡት ደን ምትክም በተያዘው ክረምት  መልሶ በችግኝ እንዲለብስ የማድረግ ስራ አከናውነዋል። በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር አሁን ላይ  330 ሺህ የሚጠጋ መሬት በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ጥብቅ ደን እንደሚገኝም ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም