እውን ፕሬዚደንት ኦባማ ከተፀፀቱ…

151

የዚህ ጽሁፍ ባለቤት መልካሙ ዘርይሁን ኣስራት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ፋኩልቲ በፕሬስ ጋዜጠኝነት በዲፕሎማ እና በሬዲዮ ጋዜጠኝነት በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቀ፤ ‘ንጉስ አርማህ’ እና ‘ህንደኬ’ የተሰኙ ታላላቅ ታሪካዊ ተውኔቶችን ጽፎ ለእይታ ያበቃ እንዲሁም ‘የኛ እድር’ የተሰኘ ሳታየር ኮሜዲ ደርሶ በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች፣ በውጭ አገር በለንደንና ዋሽንግተን ከተሞች የታየለት ታላቅ የኪነጥበብ ሰው ነው።

ወንድም ጋዳፊ ነሀሴ 26 1961 ዓ.ም. ወጣት ሊብያውያን መኮንኖችን በመምራት የቀዳማዊ ንጉስ እንድሪስን መንግስት ያለምንም ደም መፋሰስ ገልብጠው ስልጣን ያዙ፡፡ ወዲያው ‹‹አብዮታዊ እዝ ምክር ቤት›› ያቋቋመው ደርግ ዘውዳዊውን ስርዓት በማፍረስ ሊብያ አረብ ሪፐብሊክን መሰረቱ፡፡ ዓላማቸውም ‹‹ነፃነት፣ ሶሻሊዝምና አንድነት›› ናቸው አሉ፡፡

ጋዳፊ ወደ ስልጣን እንደመጡ የሀገሪቱን የተትረፈረፈ የነዳጅ ሀብቶችን በቀጥታ ለትምህርት፣ ጤናና መሰረተ ሰፊ ለሆነ የመኖርያ ቤቶች ግንባታ አዋሉ፡፡

የህዝብ ትምህርት ቤቶች በነፃ አገልግሎት እንዲሰጡ ታዘው ተግባራዊም አደረጉ፡፡ መማር ለወንድም ሆነ ለሴቶች ግዴታ መሆኑን በአዋጅ ደነገጉ፡፡ የጤና ተቋማት በመላ ሀገሪቱ ተስፋፉ፣ ያም ብቻ ሳይሆን ማናቸውም ሊብያዊ ህክምና በነፃ እንዲሆን አደረጉ፡፡

ገቢያቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሊብያውያን የመኖርያ ቤቶችን በነፃ እስከ ማግኘት የሚደርስ መብት ሰጧቸው፡፡ ከፍተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሊብያውያን እጅግ በተዋቡ አየር ማቀዝቀዣ የተገጠመላቸው ቤቶች በዚያ በረሀ ውስጥ በሰላም ይኖሩ ነበር፡፡

የበርካታ አፍሪካውያን አመታዊ የነብስ ወከፍ ገቢ አንድ መቶ ዶላር በታች በነበረበት ግዜ የሊብያውያን ነፍስ ወከፍ ገቢ ግን አስራ አንድ ሺህ ዶላር ደርሶ የነበረ ሲሆን፣ የኢኮኖሚ እድገቱ ከአፍሪካ እጅግ የላቀ ከአንዳንድ የአረብ ሀገራት ጋር ሲነፃጸር ደግሞ ከአብዛኞቹ የተሻለ እንደነበር ዓለም የሚያውቀው ሀቅ ነበር፡፡

ጋዳፊን የምእራቡ ዓለም ጥርስ ውስጥ የከተታቸው ከፍልስጤም ነፃነት ትግል ጋር ያላቸው ትስስርና ወደ ኋላ ዘመናቸው በአረቡ ዓለም የደከሙበት የአረብ ሀገራት ህብረት አልሳካ ሲላቸው ከአፍሪካውያን ጋር የጀመሩት ቁርኝት በብዙ ምእራባውያን መሪዎች ዘንድ አለመወደዱ እንደነበር በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች ይስማሙበታል፡፡

በተለይ ከያሲር አራፋት የፍልስጤም ነፃ አውጪ ድርጅት፣ ከኩባው መሪ ፊደል ካስትሮ ጋር እንዲሁም ኔልሰን ማንዴላ በሮቢን ደሴት ታስረው የደቡብ አፍሪካን አፓርታይድ ስርአትን ትግል በገንዘብና በሞራል መደገፋቸው፡፡

ወደ አውሮጳም ዘልቀው የ‹‹አየርላንድ ሪፐብሊክ አርሚን›› መደገፋቸው፣ እንዲሁም በሞሮኮ የሚንቀሳቀሰውን ምእራብ ሰሀራን ነፃ ለማውጣት የሚታገለውን ፖሊሳሪዮን ግንባር መደገፋቸው  የምእራቡ ዓለም የስለላ ተቋማት ጋዳፊን አፈር ለማላስ ቀን እንዲጠብቁ አድርጓቸዋል፡፡

በተለይ በተለይ ሀሙስ ሀምሌ 20 2003 ዓ.ም. በካምፓላ ኡጋንዳ በተደረገው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይ ጋዳፊ እንደ ሁልግዜውም ተዋጊ ባህርያቸው ለአመታት ሲጥሩበት የነበረውና የተባበሩት የአፍሪካ መንግስት ምስረታ ህልማቸውን አስመልክተው የተወሰኑ አለማቀፍ ሚድያዎችን ጠርተው መግለጫ ሰጡ፡፡

በጉባኤው ላይም ይኸው ሀሳባቸው ጎልቶ እንዲሰማ የቻሉትን ያህል ጣሩ፣ መሪዎችን ለማግባባት ሞከሩ ግን በዚያን ወቅት የሶማሊያው ቀውስ እንዳዲስ የፈነዳበትና የሱዳኑ መሪ ኦማር አል በሽር በዳርፉር ምክንያት ዘሄግ በሚገኘው የዓለም ፍርድ ቤት የተከሰሱበት ወቅት ስለነበር የአፍሪካ መሪዎች የጋዳፊን ሀሳብ ብዙ ሳይነጋገሩበት ቀሩ፡፡

ከጉባኤው በኋላም እንዲሁ ጋዳፊ የአፍሪካ መንግስት ምስረታ በተያዘለት ሁኔታ እየተከናወነ ነው፡፡ ብለው ለጋዜጠኞች መልሰው ተናገሩ፡፡ በጉዳዩ ተስፋ አለመቁረጣቸውን ለዓለም አሳወቁ፡፡

አያይዘውም ከተትረፈረፈ ሀብታቸው ለአፍሪካ አንድ መንግስት መመስረት እንደሚያውሉ አወጁ ይህንንም ለማሳካት የአፍሪካ መሪዎችን በገንዘብ ለመደለልና ለማግባባት አዋሉት፡፡

በአፀፋው ግን አፍሪካውያን መሪዎችና አማካሪዎቻቸው ከጋዳፊ ገንዘብ እንጂ ከሀሳባቸው ብዙም አልተግባቡም፡፡ ስልጣን አጣጥመው ያልጠገቡ፣ ጨቅላ መሪዎች በምእራቡ ዓለም ፕሮፓጋንዳ ስለደነዘዙ መስሚያ ጆሮ አልነበራቸውም፡፡ ጭራሽ ምእራባውያን ጋዳፊን በአየርም ሆነ በምድር ጦር መከራቸውን ሲያሳዩአቸው አንድም የአፍሪካ መሪ ተቃውሞውን ለማሰማት የፈቀደ አልነበረም፡፡ ሁሉም ማን ከሳቸው ቀጥሎ እንደሚደበደብ ስላላወቀ ዝምታን መረጡ፡፡

ነሀሴ 14 2003 ዓ.ም. የሊብያ አማፂያንና የኔቶ ጀቶች በሙአመር ጋዳፊ ላይ ጥቃት ጀመሩ፡፡ በዚሁ ዕለት ጋዳፊ ለህዝባቸው ተናገሩ ‹‹ምዕራባውያን ዳግም ቅኝ ሊገዙህ ከውስጥም ከውጭም ወረራ ጀምረዋል፡፡ መላ ሊብያውያን ተነሱ ሀገራችሁን ጠብቁ…›› ብለው ነበር፡፡

ከሁለት ወር በኋላ ጋዳፊ ከተደበቁበት የትውልድ መንደራቸው ሲርት ተጎትተው በዓለም ፊት በቴሌቪዥን መስኮት በጥፊና ጉሽሚያ እየተንገላቱ አናታቸው ተነድሎ ተገደሉ፡፡ አፍሪካን አንድ የማድረግ ህልማቸው ብቻ ሳይሆን የገነቧት ውቧ የበረሀ ገነት የነበረችው ሊብያም አብራ አፈር ድሜ በላች፡፡

ከኔቶ ጋር ግንባር ፈጥረው ሊብያን ሲያስደበድቡ የነበሩት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የጋዳፊን ሞት ሲሰሙ የአሁኑ ፕሬዚደን የዛኔው ምክትላቸው ጆ ባይደን እንዲሁም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውና  ሂላሪ ክሊንተን ጋር በመሆን በደስታ ጽዋቸውን አነሱ፡፡

በጋዳፊ አንፃር የተከተሉት የውጊያ ስልት ተወደሰላቸው፡፡ በቀላል ኪሳራ ድል ማግኘታቸው ተሞካሸ፡፡ ቀድመው ከነበሩት ፕሬዚዳንቶች በተለየ አሜሪካውያን ወታደሮችን ልከው ሳይሆን ከጀርባ የኔቶን ሀይሎች በአየር ሀይል በመደገፍ የተገኘ ድል ተብሎ ተንቆለጳጰሰ፡፡

ከጋዳፊ መወገድ በኋላ ዓለም የሚያውቃትን ሊብያን በዚህ አጭር ጽሁፍ ገልፆ መናገር እጅግ ከባድ እንደሆነ አንባቢ ይረዳል፡፡ በቀላሉ በበይነ መረብ፣ ፌስ ቡክና ትዊተር ላይ የሚለጠፉትን ፎቶዎች አካላዊ አሁናዊና የቀደመው ሊብያ ምን እንደምትመስል በሚገባ ይገልፃሉ፡፡ በአስር ዓመት ግዜ ውስጥ የበረሀ ገነት የነበረችውን ሀገር ፍርስራሽና አመድ አድርገዋታል፡፡

ህፃናት ዜጎቿ አፈር ከሆኑት ፍርስራሽ ቤቶቻቸው በር ላይ ተኮልኩለው ሲታዩ አንጀት ይበላሉ፣ እነዛ ማቀዝቀዣ የተገጠመላቸው ምርጥ መኖሪያዎችን ፈልጎ ማግኘት አሁን ላሉት ሊብያውያን ምጸት ነው፡፡

የነዳጅ ሀብቷን ለመቀራመት በስመ ሊብያውያን የአውሮጳና አሜሪካን ኩባንያዎች በቅጥር ነብሰ ገዳይ ዱርዬዎች የሚፋለሙባት ምድር ሆና እያየናት ነው፡፡

የገዛ ልጆቿ በምእራብያውያኑ አይዞህ ባይነት ሀገራቸውን አወደሙ፡፡ የቀደመችውን ሊብያን በተረት ተረት እንጂ በቅርቡ እንደማያገኟት ለማወቅ አስር አመት ፈጅቶባቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ የሀገሪቱ አንጡራ የነዳጅ ዘይት ሀብት የአውሮጳና አሜሪካ ኩባንያዎች እንጂ የሊብያውያን አይደሉም፡፡

ህክምና፣ ትምህርትና ጤና በነፃ የሚገኙባት ሊብያ አሁን እነዚህን መሰረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎቶች ለማሟላት የማትችል የሰቆቃ ምድር ሆናለች፡፡ የመንግስት ሰራተኞችን ደሞዝ ሙሉ ቀርቶ ግማሹን ለመክፈል የተቸገሩባት ሀገር፣ ሊብያ፡፡

መንግስት አልባዋ ሊብያ አፍሪካውያን ወደ አውሮጳ ለመሰደድ ድንበሮቿን እንደፈለጉ የሚወጡበትና የሚገቡበት ኦና በር ሆናለች፡፡ ባሪያ ፈንጋዮችም በሊብያ በርሀ የሚርመሰመሱባት የጉድ ሀገርም ሆናለች፡፡

አክራሪ የእስልምና ቡድኖችም በሊብያ ከትመው እንዳሻቸው አንገት የሚቀሉበት ሀብት የሚገፉበት፣ ደካማውን መንግስት በጦር ለመጣልም የሚገዳደሩበት ቦታ ሊብያ ነው፡፡

ይሄ ሁሉ ውርጅብኝ የወደቀባትን ሊብያ አስመልክቶ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሰጡ በተባለው ቃለ-መጠይቅ በስልጣን ዘመናቸው በሊብያ ያደረጉትን ጣልቃ ገብነትና እንደ ገዛ  ልጃቸው ይመለከቷቸው የነበሩትን ጋዳፊን ከስልጣን ለማስወገድ ጦር መምዛቸው እንደሚጸጽታቸው ተናግረዋል፡፡

ኦዎ! ሊብያ ላይ የሆነውን ማንም መልሶ እንደነበረ ለማድረግ የሚችል አንዳች ምድራዊ ሀይል የለም፡፡የፈሰሰ ውሀ አይታፈስም ሌላ የጥፋት ሰቆቃ በአፍሪካ እንዳይደርስ ግን ባራክ ኦባማ ድምጻቸውን ማሰማት ይገባቸዋል፡፡

ጸጸት የሰው ልጆች የተቀደሰ ባህርይ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ግን ጸጸቱ የእውነት የሚሆነው ደግሞ ተመሳሳይ ጥፋት እንዳይደርስ ለማድረግ ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም የሀገራቸው መንግስት እጁን እንዲሰበስብ በመምከር ማሳየት ይገባቸዋል፡፡

ያንዜ ምክትላቸው የነበሩት ጆባይደን የአሁኑ የአሜሪካን ፕሬዚደንት ከኢትዮጵያና ኤርትራ አንፃር እየተከተሉት ያለው ፖሊሲ ምንም ያልተቀየረና ጭራሽ ከመላው አፍሪካ ጋር ጦር ለመማዘዝ ያሰቡ እስኪመስል ድረስ የእውር ድንብራቸውን እየጋለቡ ይገኛሉ፡፡

በመሆኑም ኦባማ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያን በዋሽንግተን ዲሲ ነጩ ቤተ-መንግስት ፊት ለፊት በሚያደርጓቸውን የተቃውሞ ሰልፎች ላይ መገኘት ይገባቸዋል፡፡ የትግል አጋርነታቸውን በማሳየትም ፀፀታቸውን ተጨባጭና የእውነት መሆኑን እኛ አፍሪካውያንን ዐይን ዐይናችንን በመመልከት ሊነግሩን ይገባል፡፡ እኛም ሆንን ሊብያውያን ከምር ይቅር የምንላቸው ይሄንን ሲያደርጉና ዳግም አሜሪካን በኢትዮጵያም ሆነ በተቀረው አፍሪካ ጣልቃ ለመግባት የምታደርገውን የተሳሳተ እርምጃ ለማስቆም አጋርነታቸውን የገለጹ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎም ስልቻ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም