በምዕራብ ጎንደር ዞን ከ23ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በጥጥ በማልማት ለኢንዱስትሪ ለማቅረብ እየተሰራ ነው

103

መተማ ፤ መስከረም 22/2014(ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ከ23 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በጥጥ ሰብል በማልማት ለጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ግብዓት ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በዞኑ ያለው መልክአምድርና የአየር ንብረት ለእርሻ ኢንቨስትመንት የተመቸ መሆኑ ተመልክቷል።

በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ሞገስ ጋሹ ለኢዜአ እንዳሉት ፤ አካባቢው ለዘርፉ ልማት ባለው አመቺነት ለጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች በግብአትነት የሚቀርብ ጥጥ ለማምረት በአርሶ አደሩና በባለሃብቶች 23ሺህ 700 ሄክታር  መሬት ለምቷል።

ከዚህም ውስጥ 11ሺህ 700 ሄክታር የሚሆነው በባለሃብቶች፤  ቀሪው በዞኑ በሚገኙ አርሶ አደሮች የለማ መሆኑን ነው ያመላከቱት።

"በአሁኑ ወቅት የአረም፣ የኩትኳቶ፣ የተባይ መከላከልና ሌሎች የእንክብካቤ ሥራዎች በመሰራቱ ሰብሉም በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል፤ከለማውም  450ሺህ ኩንታል ምርት ይጠበቃል" ብለዋል።

በመተማ፣ ምዕራብ አርማጭሆ እና ቋራ ወረዳዎች ከ10ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ዝግጅት ተደርጎ እንደነበር አውስተው፣ በሱዳን ወራሪ ሃይል ምክንያት መሬቱ ጦም ማደሩን ጠቅሰዋል።

በአርሶ አደሩና ባለሃብቱ እየተመረተ ያለው የጥጥ ምርት በገንዳ ውሃ ከተማ በቅርቡ ሥራ ለጀመሩት ሦስት የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካዎች በግብአትነት እንደሚቀርብም አስታውቀዋል።

እንደባለሙያው ገለጻ፤  የጥጥ ምርታማነትን ለማሳደግ ሦስት ኩንታል ምርጥ ዘር በዞኑ በኩል ሲቀርብ ቀሪውን ደግሞ ከጥጥ መዳመጫ ፋብሪካዎች መጠቀም ተችሏል።

በመተማ ወረዳ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ ጀጃው አብርሃ በበኩላቸው፤ በደለሎ እርሻ ልማት ጣቢያ እያለሙት ካለው 61 ሄክታር መሬት ውስጥ 10 ሄክታሩ በጥጥ ልማት የተሸፈነ ነው ብለዋል።

ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ መሬት ላይ 170 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን አውስተው፣ "ዘንድሮ አያያዙ ጥሩ በመሆኑ የበለጠ ምርት እጠብቃለሁ" ነው ያሉት።

በመተማ ወረዳ ሽመለጋራ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር ክብረት መንግስቱ፤  ካላቸው 10 ሄክታር መሬት ውስጥ 4 ሄክታሩን በጥጥ ሰብል መሸፈናቸውን ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት ከሁለት ሄክታር መሬት ጥጥ ልማት ያገኙትን 32 ኩንታል ምርት 110ሺህ ብር መሸጣቸውን አስታውሰው፤ ዘንድሮ በስፋት በመዝራታቸው ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይጠብቃሉ።

በገንዳውሃ ከተማ የአብዱቃድር የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ ባለቤት ሐጅ አብዱልቃድር አህመድ ፤ፋብሪካው በዓመት እስከ 120ሺህ ኩንታል ጥጥ መዳመጥ እንደሚችል ተናግረዋል።

"ፋብሪካው ከግብአት አቅራቢዎች ጋር በመተሳሳሩ ጥራት ያለው 40ኩንታል የጥጥ ዘር ለባለሃብቶችና አርሶ አደሩ በማቅረብ በስፋት እንዲያለሙ እያገዘ ይገኛል" ብለዋል።

አርሶ አደሩና ባለሃብቱ የሚያመርተውን የጥጥ ምርት ተረክበው እሴት ጨምረው በማምረት ለጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ለማስረከብ እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት በዞኑ 19ሺህ ሄክታር መሬት በጥጥ ለምቶ ከ320 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት በመሰብሰብ  ለኢንዱስትሪዎች መቅረቡን ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም