መንግስት ዓለም አቀፍ ተቋማት በአገሩ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ መከላከል ተቀዳሚ ተግባሩ ነው

103

መስከረም 22/2014 (ኢዜአ) መንግስት ዓለም አቀፍ ተቋማት በውስጥ ጉዳዩ ጣልቃ እንዳይገቡ መከላከልና የአገሩን ሉዓላዊነት ማስከበር ቀዳሚ ተግባሩ መሆኑን የሕግና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ገለጹ።

የኢትዮጵያ መንግስት በውስጥ ጉዳዬ ጣልቃ ገብተዋል ያላቸውን ሰባት የተመድ ሠራተኞች በ72 ሠዓታት አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ማሳሰቡ ይታወቃል።

ኢዜአ የውሳኔውን አንድምታና እርምጃው ከአገር ሉዓላዊነት አንፃር የሚኖረውን ፋይዳ በተመለከተ ከሕግ ባለሙያና አማካሪ አቶ ፋሲል ስለሺ እና ከፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር ደመቀ አጪሶ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳዬ ጣልቃ ገብተዋል ባለቻቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሠራተኞች ላይ የወሰደችው እርምጃ ተገቢና ዓለም አቀፍ ሕጎችም የሚደግፉት መሆኑን ገልጸዋል። 

የሕግ ባለሙያና አማካሪ አቶ ፋሲል ስለሺ፤ መንግስት የአገሩን ሉዓላዊነት የማስከበርና ዓለም አቀፍ ተቋማት በውስጥ ጉዳዩ ጣልቃ እንዳይገቡ የመከላከል ስራ ተቀዳሚ ተግባሩ ነው ብለዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የትኛውም አገር ሆነ ዲፕሎማት የተሰጠውን ተልዕኮ ትቶ በአንድ አገር የውስጥ ጉዳይ  ገብቼ እንደፈለግሁ እሆናለሁ ማለት እንዳይችል ዓለም አቀፍ ሕጎች እንደሚያግዱት ያብራራሉ።

ይህም በተባበሩት መንግስታት ማቋቋሚያ ቻርተር ላይ በአንድ አገር የውስጥ ጉዳይ አለመግባት በግልጽ የተቀመጠ ዓለም አቀፍ ሕግ ሰለመሆኑ ነው ያስቀመጡት።

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት በጣም ታገሰ፣ ዘገየ ከመባል በቀር የወሰደው እርምጃ ተገቢና ዓለም አቀፍ ሕግጋቶችም የሚደግፉት ነው ብለዋል።

ውሳኔው ትክክለኛና የአገሪቷን ሉዓላዊነት ያስከበረ መሆኑን የገለፁት የሕግ ባለሙያው መንግስት በዓለም አቀፍ ሕግም ተቀባይነት ያለው አሰራር ተግባራዊ ማድረጉ የሚበረታታና ሌሎችም በዚህ ሕገወጥ ተግባር ለተሰማሩ ዓለም አቀፍ አካላት አስተማሪ ውሳኔ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ታሪክ አኩሪ ገድል የፈፀመች አገር መሆኗን እና የዓለም አቀፍ ህጎችንም አክባሪ ሰለመሆኗ ያሰመሩበት የሕግ ባለሙያው አሁን የወሰደችው እርምጃ  እጅግ በጣም ታግሳ ስለመሆኑ ነው የገለፁት።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የፈረጀውን ህወሓትን ለመርዳት ጥረት ማድረግ በዓለም አቀፍ ሕግ ከፍተኛ ወንጀል መሆኑን ጠቅሰው በፐርሶና ነን ግራታ መርህ /Persona non grata/ መሰረት ሉዓላዊነት የጣሰ ዲፕሎማት መንግስት በወሰነው መሰረት አገሪቱን ለቆ ለመውጣት ይገደዳል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ዶክተር ደመቀ አጪሶ በበኩላቸው አገራት በየትኛውም መስፈርት ሉዓላዊና የሚያወጧቸው ሕጎችም በሁሉም ላይ ተፈፃሚ ናቸው ብለዋል።

በቪየና ኮንቬንሽን መሰረት ለዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ስራ ሲባል አገራት ወደውና ፈቅደው አንዳንድ አካላት ነፃ እንዲሆኑ ፈቃዳቸውን ቢሰጡም በስምምነቱ መሰረት በአንድ አገር የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት እንደማይቻል ይደነግጋል ይላሉ።

በስምምነቱ አንድ ዲፕሎማት የአገሪቷን ሕግ፣ ስርዓትና ወግ ተከትሎና አክብሮ መስራት እንደሚገባው ነው የተናገሩት።

ስምምነቱ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እንዳይኖርበትና ስራውን በነፃነት እንዲሰራ የሚሰጥ ሕግ እንጂ እንደፈለጉ መሆን አያስችልም ብለዋል።

ማንኛውም ዲፕሎማት ከስርዓት ውጭ በሆነ መንገድ በአገራት ጉዳይ ጣልቃ የሚገባ ከሆነ በፐርሶና ነን ግራታ መርህ ኢትዮጵያ እንደወሰደችው እርምጃ የሚወሰድበትና ይህም በዓለም ታሪክ ሲተገበር የኖረ ነው ብለዋል።

ግዴታዎችና ስርዓቶችን አክብሮ ያልተንቀሳቀሰ ዲፕሎማት በማንአለብኝነት እንደፈለገ መንቀሳቀሰ አይችልም ለህልውና አደጋ በሆነ ጊዜ እርምጃው ሊወሰድበት ይችላል ነው ያሉት።

አገራት በውስጥ ጉዳዬ ጣልቃ ገብተዋል ያሉትን የዲፕሎማቲክ አካላት ላይ ከአገር እንዲወጣ የማድረግ መብት እንዳላቸው ገልፀው፤ የተፈቀደላቸውን ሠዓት ካሳለፉ እንደማንኛውም ዜጋ በአገሪቷ ሕግ ይጠየቃሉ ነው ያሉት።

ኢትዮጵያም ይህንኑ መብቷን ነው የተጠቀመችው ያሉት ዶክተር ደመቀ፤ ይሁን እንጂ አሁን ጥያቄ የሚያነሱ ሃያላን አገራት ለሕጉ ተገዢ  ባለመሆናቸው ምክንያት ያልሰከነ መግለጫ ነው ያወጡት ብለዋል።

እነዚህ አካላት በዚህ ሳቢያ በአገሪቷ ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን ጫና መንግስት ቀደም ብሎ አገናዝቦና አስቦበት መወሰኑን ግምታቸውን ያሰቀመጡት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ጫናውን ለመቋቋም ሁሉም ከመንግስት ጎን ሊቆም ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም