በምዕራብ ጎንደር ዞን በህገ-ወጥ መንገድ ተይዞ የነበረን 4 ሺህ 890 ሄክታር መሬት በማስመለስ ለወጣቶች ተሰጠ

110
መተማ ነሀሴ 10/2010 በምዕራብ ጎንደር ዞን በህገ-ወጥ መንገድ በግለሰቦች ተይዞ የነበረን 4 ሺህ 890 ሄክታር የእርሻ መሬት በማስመለስ መሬት ለሌላቸው ወጣቶች መሰጠቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡ በመምሪያው የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ ወርቁ ዘውዱ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በህገ ወጥ መንገድ የተያዘን መሬት በማስመለስና የወል መሬትን በመለየት ስራ ለሌላቸው ወጣቶች ተላልፏል። መሬቱን በማስመለስም በመተማ፣ ቋራና ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳዎች የሚገኙ አንድ ሺህ 478 ወጣቶች በእርሻ ስራ ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ተናግረዋል። ለወጣቶች ከተላለፈው መሬት ውስጥ ከ3 ሺህ 800 ሄክታር መሬት ለወጣቶቹ በቋሚነት በግል የተሰጣቸው ሲሆን ቀሪው መሬት በቡድን ለተደራጁ ወጣቶች በአምስት አመት የኮንትራት ውል እንዲሰጣቸው መደረጉን ገልፀዋል። በተናጠልም ሆነ በቡድን የተሰጠው መሬት ውስጥም አራት ሺህ 600 ሄክታር የሚጠጋው በህገወጥ ተይዞ የነበረ መሆኑን አስታውሰው 290 ሄክታሩ ደግሞ የወል መሬት ነው። ወጣቶቹ በተሰጣቸው መሬት ከእርሻ ስራ በተጨማሪ በእንስሳት ማድለብና እርባታ ስራ መሰማራታቸውን አቶ ወርቁ አብራርተዋል። በመተማ ወረዳ ‹‹ቱመት›› አካባቢ በቡድን ተደራጅተው መሬት ከተሰጣቸው መካከል ወጣት መካሻው አበራ እንደተናገረው ከዚህ ቀደም ምንም አይነት ስራ እንዳልነበረው አስታውሶ አሁን በተሰጣቸው 80 ሄክታር መሬት በእርሻ ስራ ተሰማርተው ሰሊጥና ማሽላ ማልማታቸውን ገልጿል። ማህበራቸው ስምንት አባላት ያሉት ሲሆን በተሰጣቸው የእርሻ መሬት ውጤታማ ለመሆን ተግተው እየሰሩ ሲሆን ከመንግስትም ተገቢው ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነም አስታውቋል። “መሬቱን አልምቼ ራሴን እንድለውጥ መንግስት ካደረግልኝ ድጋፍ በተጨማሪ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ማግኘቴ ጠንክሬ በመስራት ውጤታማ እንድሆን ያግዘኛል” ያለው ደግሞ በቋራ ወረዳ አጋም ውሃ ቀበሌ የእርሻ መሬት ባለቤት የሆነው ወጣት እንዳለው ድረስ ነው፡፡ ወጣቱ አያይዞ እንደገለፀው ከተሰጠው 10 ሄክታር መሬት ውስጥ ስምንት ሄክታሩን በሰሊጥ ቀሪውን ደግሞ በማሽላ ዘር መሸፈኑን ተናግሯል፡፡ በዞኑ በዚህ የመኸር ወቅት 391 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያየ የሰብል ዘር በመሸፈን ከ5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም