አገራዊ የስጋት ተጋላጭነት ጥናት ሪፖርት ይፋ ሆነ

928

መስከረም 21 /2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሁለተኛው አገራዊ የስጋት ተጋላጭነት ጥናት ሪፖርት ይፋ ተደረገ።

አንድ ዓመት ከመንፈቅ የፈጀው የዚህ አገራዊ ሪፖርት ማብራሪያ መርሐ ግብር  እየተካሄደ ነው።

በሰላም ሚኒስቴርና የዓለም ባንክ ትብብር ሪፖርቱ ይፋ የተደረገ ሲሆን የሁለቱ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች፣ ሚኒስትሮችና የፋይናንስ ዘርፍ ተዋንያን ተገኝተዋል። 

በሰላም ሚኒስቴር የፋይናንስ ደህንነት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለ፤ የፋይናንስ ወንጀሎች ካልተገቱ ለአገር ሕልውና አደጋ በመሆናቸው ከሽብርተኝነት ተለይተው አይታዩም ብለዋል። 

ጥናቱም ይህን የችግር ተጋላጭነት ለመለየት የተደረገ ስለመሆኑ አንስተዋል።

የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል አዲሱ መንግስት ከሚያከናውናቸው ቁልፍ ተግባራት መካከል አንዱ ወንጀልን መከላከል እና መቆጣጠር መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለዚህም የፖሊሲ ግብአት የተገኘበት ጥናት ሲካሂድ ቆይቶ መጠናቀቁን ገልፀዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተቋቋመው ብሄራዊ ምክር ቤት የዛሬ ሁለት አመት ባስቀመጠዉ አቅጣጫ መሰረት በህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ እና በተፈጥሮ አካባቢ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የሚገኙበትን ደረጃ ለማጥናት እና አለም አቀፍ ግዴታዎችን ለማሟላት የተጀመረው ስራ በርካታ የመንግስት፣ የግል እና የሙያ ማህበራትን አካቶ ለውጤት በቅቷልም ብለዋል።

ይህ የስጋት ተጋላጭነት ጥናት በሰላም ሚኒስቴር መሪነት ከአለም ባንክ ጋር በመተባበር የተከናወነ ሲሆን በርካታ ተግዳሮቶችን አልፎ በአንድ አመት ተኩል ጊዜ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በውጤቱም በአገራችን የሚገኙ የወንጀል አመንጪ ክፍተቶችን፣ ወንጀሎችን እንዲሁም ሌሎች አስቻይ ሁኔታዎችን በስፋት እና በጥልቀት ለማየት የቻልንበት ሲሆን መንግስት እነዚህን

ወንጀሎች ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያስችሉትን ጠንካራ ፖሊሲዎች ለማውጣት እና አሰራሮችን ለማስተካከል የሚያግዙ ማስረጃዎችን ስለሚሰጥ በሂደቱም፣ በውጤቱም ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው ሂደት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰአት መሳሪያ ታጥቀው አገርን ለማፍረስ የሚሰሩ ሃይሎች እኩል የኢኮኖሚ

ኣሻጥር በመፈጸም የኑሮ ውድነትን በማስከተል፣ ኢኮኖሚን ለማዛባት እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመፍጠር የውንብድና አሰራሮች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን

የዚህ ጥናት ውጤት የወንጀል አስቻይ ሁኔታዎችን በሚገባ ማክሰም እና መቆጣጠር እንዲቻል የሚያግዙ ይሆናሉ ብለዋል።

በሂደቱ ከ19 ፌዴራል መንግስት ተቋማት የተውጣጡ የቴክኒክ አባላት፣ ከመንግስት የልማት ድርጅቶች እና ከሙያ ማህበራት ጋር በመተባበር 60 አባላትን አካተው ጥናቱ አለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መጠናቀቁንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ጥናቱ በ10 ክፍሎች የተሰራ በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ዙሪያ ያሉ ስጋት እና ተጋላጭነቶችን በሙሉ ለመሸፈን የሞከረ ነውም ብለዋል፡ 

በጥናቱ ከማዕድን ዘርፍ እስከ ሪል ስቴት፣ ከሰነዶች ምዝገባ እስከ መኪና አስመጪዎች፣ ከባንኮች እስከ ኢንሹራንሶች፣ ከብድርና ቁጠባ ተቋማት እስከ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተዳሰዋል፤ የሕግ ክፍተቶችም ተለይተዋል ነው ያሉት፡፡

እነዚህን ወንጀሎች ለመከላከል የሚያስችሉ ሕጎችን የማውጣት እና ተቋማትን የማስተካከል ስራ በቀጣይ አንደሚሰራም ጠቁመዋል።