የአውሮፓ ህብረት፤ በኢትዮጵያ አዲስ ከሚመሰረተው መንግስት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ ነው

96

መስከረም 21/2014 (ኢዜአ) የአውሮፓ ህብረት፤ በኢትዮጵያ አዲስ ከሚመሰረተው መንግስት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ተናገሩ።

ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በኢትዮጵያ የተሾሙ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ተቀብለዋል።

ፕሬዚዳንቷ  በኢትዮጵያ የተሾሙ የታይላንድ፣ የኒውዝላንድ፣ የዴንማርክ፣ የጅቡቲ፣ የአውስትራሊያ፣ የአውሮፓ ህብረት እና የግብጽ አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ  የተቀብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ፤ የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ አዲስ ከሚመሰረተው መንግስት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

"ወደ ኢትዮጵያ የመጣነው በውነተኛ የአጋርነት መንፈስ ነው" ያሉት አምባሳደሩ በተለይም በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍንና ችግሮች እንዲፈቱ ትብብርና እገዛ እናደርጋለን ብለዋል።

የሹመት ደብዳቢያቸውን ለፕሬዘዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የሰጡት የተለያዩ አገራት አምባሰደሮችም ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

በተለይም በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም፣ በንግድና ኮቪድ 19ኝን በመከላከል ረገድ አብረን ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል አምባሳደሮቹ።

አምባሳደሮቹ ከፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር ያደረጉትን ውይይት የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ፕሬዘዳንቷ  የኢትዩጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ለአምባሳደሮቹ ማስረዳታቸውን ገልጸዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ ከአገራቱና ከአለም አቀፍ ተቋማት ጋር ግንኙነቷን ለማጠመናከር ያላትን ቁርጠኝነትና ፍላጎት አብራርተውላቸዋል ብለዋል።

አምባሳደሮቹም ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ዘርፎች የትብብር ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ለፕሬዝዳንቷ መግለፃቸውን አምባሳደር ዲና ጠቅሰዋል።

በተለይም በአውሮፓ ህብረትና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ትብብር ይበልጥ ለማሻሻል እንደሚሰሩ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ አረጋግጠዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም