ለዘማችና አቅም ለሌላቸው ቤተሰብ ልጆች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

90

ደብረ ብርሃን/ ሰመራ፤ መስከረም 21/ 2014 (ኢዜአ) በሰሜን ሽዋ ዞን ለዘማች ቤተሰብ ተማሪ ልጆች 329 ሺህ ብር ግምት ያለው የትምህርት ቁሳቀስ ድጋፍ ተደረገ።

ኢትዮ-ቴሌኮም የሰሜን ምስራቅ ምስራቅ ሪጅን ቅርንጫፍ  በአፋር ክልል ዱብቲ ከተማ ለሚገኙ ተማሪዎች የደብተር ድጋፍ አድርጓል።

በሰሜን ሸዋ ዞን ድጋፉን ያደረጉት ስቲሊ አር.ኤም. አይ፣ አስመን እና ታይስ ሃላፊነታቸው የተወሰኑ የግል ድርጅቶች ናቸው። 

ታይስ ሃላፊነቱ የተወሰ የጨርቃጨርቅ አምራች ድርጅት ተወካይ አቶ ወልዴ ጌታቸው በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንዳሉት፤ ባለሃብቱ አልምቶ ሃገር ማሳደግ የሚችለው ዘላቂ ሰላም ሲኖር ነው።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በንጹን ላይ እየፈፀመ ያለው ግፍና በደል፤ ሀገርን የማፍረስ ሴራ በአጭር ጊዜ እንዲቋጭ መደጋገፍና መተባበር የግድ መሆኑን ተናግረዋል።

"የሀገር ህልውናን ለማስከበር በግንባር እየተፋለሙ የሚገኙ የዘማቾችን ቤተሰቦች በሁለንተናዊ መንገድ ማገዝ ይገባል" ብለዋል።

"ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከድርጅቶቹ ተወካዮች ጋር በመነጋገር በ329 ሺህ ብር የተገዛ ደብተር፣ እስክርቢቶ እና ሌሎች የትምህርት ቁሶችን ለተማሪዎች አበርክተናል" ሲሉም አክለዋል። 

ለህልውና ዘማች ቤተሰቦች የሚደረገው ድጋፍ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያስታወቁት።

የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ የሚሹ 4 ሺህ 972 የዘማች ልጆች መኖራቸውን የገለጹት ደግሞ የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ዓይነኩሉ አበበ ናቸው።

"የተደረገው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ የህፃናቱን ስነ ልቦና ለመገንባት ፋይዳው የጎላ ነው" ብለዋል።

ድጋፉ ለዘማች ቤተሰቦች በትክክል እንደሚደረስ ገልጸው፣ በቀጣይም ባለሃብቶች የጀመሩትን መልካም ጥረት ማጠናከር እንዳለባቸው አመልክተዋል።  

በሌላ በኩል ኢትዮ-ቴሌኮም የሰሜን ምስራቅ ምስራቅ ሪጅን ቅርንጫፍ  በአፋር ክልል ዱብቲ ከተማ ለሚገኙ 1ሺህ 500 ተማሪዎች የመማሪያ ደብተር ድጋፍ አድርጓል።

የቅርንጫፉ ኦፕሬሽን ዳይሬክተር አቶ አብዱ መሀመድ ድጋፉን ሲያስረክቡ እንደተናገሩት የድጋፉ ተጠቃሚዎች ገቢያቸው ዝቅተኛ የሆነ ቤተሰብ ልጆች ናቸው።   

"ኢትዮ-ቴሌኮም ዘመናዊ የመገናኛ አውታርን በመላ ሀገሪቱ ከማስፋፋት ባሻገር ማህበራዊ ሀላፊነቱን ለመወጣት በተለያዩ ዘርፎች ድጋፍ እያደረገ ይገኛል" ብለዋል።

ተቋሙ "አንድ ደርዘን ደብተር ለአንድ ተማሪ" መሪ ሀሳብ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦችን ለማገዝ ዱብቲ ከተማ ለሚገኙ ተማሪዎች 1ሺህ 500 ደርዘን ደብተር ማበርከቱን ተናግረዋል።

የዱብቲ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አሊ ከሎይታ፤ ለተደረገው ድጋፍ በከተማ አስተዳደሩና በተማሪ ቤተሰቦች ስም ምስጋና አቅርበዋል።

ኢትዮ-ቴሌኮም የመማሪያ ቁሳቁስ ሲያደርግ ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነም ነው የጠቆሙት።

በድርጅቱ የተደረገው ድጋፍ በከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ ወላጆቻቸውን በሞት ላጡ ታዳጊ ህጻናትና እና ደብተር ለመግዛት አቅም ለሌላቸው ወላጆች እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ባለሃብቶች መሠል ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም አቶ አሊ ጥሪ አቅርበዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው የተማሪ ወላጆች መካከል ወይዘሮ ፍጡማ ዳውድ፤ በአሁኑ ወቅት ለአንድ ተማሪ ደብተር ለመግዛት ከአቅም በላይ እየሆነባቸው መምጣቱን ተናግረዋል።

"በተለይ እንደ እኔ እንጀራ እየሸጡ ልጆች ለሚያሳድጉ ወላጆች ከባድ ነው" ያሉት ወይዘሮ ፋጡማ፤ የተደረገላቸው ድጋፍ ጫናውን እንደሚቀንስላቸው ገልጸዋል።

ያለአባት የሚያሳድጉትን አንድ ልጃቸውን ለማስተማር ሁሌም ትምህርት ሲከፈት እንደሚጨነቁ የተናገሩት ደግሞ ሌላው የድጋፉ ተጠቃሚ ወይዘሮ ጀሚላ አሊ ናቸው።

በድርጅቱ የተደረገላቸው ድጋፍ ችግራቸውን እንደሚያቃልላቸው በመግለጽ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም