በዘንድሮው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር ሁለት ድርጅቶች ድጋፍ የደረግላቸዋል

245

መስከረም 21/2014 (ኢዜአ) በዘንድሮው የታላቁ ሩጫ ውድድር ለሁለት ድርጅቶች ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር ኃላፊ ተናገሩ።

የውድድሩ ኃላፊ አቶ ዳግም ተሾመ፤ መርሃ ግበሩንና የሚደረገውን ድጋፍ በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ከመርሃ ግብሩ ከሚገኘው ገቢ በዚህ ዓመትም ድጋፍ ለሚሹ ሁለት የተለያዩ ድርጅቶች ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

ከዚሁ መርሃ ግብር ከሚገኘው ገቢ ለግሬስ ልጆችና ቤተሰቦቻቸው ማዕከል እንዲሁም የወጣቶች አትሌቲክስ ፕሮጀክት ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

ለድጋፉ እገዛ ለማድረግ የታላቁ ሩጫ ቲሸርት በመሸጥ ላይ መሆኑን ገልፀው፤ እስካሁን ያልገዙና እርዳታውን ለማድረግ ፍላጎቱ ያላቸው ሁሉ ከዛሬ ጀምሮ በአሞሌ በኩል መግዛት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

በዘንድሮው ዓመት ”ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ” በሚል መሪ ሃሳብ ሩጫው የሚካሄድ መሆኑንም ተናግረዋል።

ባለፉት 16 ዓመታት ”ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ” በሚል መርህ በተካሔደው ሩጫ ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ መሰበስቡን አስታውሰዋል።

የተሰበሰበው ገንዘብም ድጋፍ ለሚሹ 32 የተለያዩ ድርጅቶች መከፋፈሉን ጠቅሰዋል።

የዘንድሮው አመት የ10 ኪሎ ሜትር የታላቁ ሩጫ መርሃ ግብር ህዳር 5 ቀን 2014 ዓ.ም ይካሄዳል።