በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ማጣጣሚያ ፕሮክጀት ለመተግበር ወደ ስራ ተገብቷል

128

አዳማ መስከረም 21/2014 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለውን የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ማጣጣሚያ ፕሮጀክት ከ100 ሚሊዮን ብር በጀት ለመተግበር ወደ ስራ መገባቱ ተገለጸ።
ፕሮጀክቱ  በአዳማ ከተማ  በተካሄደ መድረክ ይፋ በተደረገበት ወቅት፤ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለውን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን ለማገዝ የሚያስችል መሆኑ ተመልክቷል።

የደን፣ አካባቢና አየር ንብረት ለውጥ  ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ እንዳሉት፤ ዘላቂ ልማትና ዕድገትን ማረጋገጥ የሚቻለው  ከአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ነጻ የሆነና ችግሩን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ ሲገነባ ነው።

እየተከናወነ ያለው የአረንጓዴ ልማት ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ውጤታማነት ቁልፍ ሚና እንዲኖረው የመተግበሪያ ስልቶች መንደፋቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ኮሚሽኑ ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅቶችን በመቅጠር የአየር ንብረት ለውጥ የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ ሰነድ አዘጋጅቶ ለተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን መላኩን አስረድተዋል።

"የዓለም አረንጓዴ ቴክኖሎጂ ለመተግበር ሀገራዊ የማጣጣሚያ ፕሮጀክት ለመተግበር የቅድመ ዝግጅት ስራ ተጠናቆ 18 የማጣጣሚያ ስልቶችን የያዘ ዕቅድ አዘጋጅተን ለመተግበር ወደ ስራ ገብተናል" ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችና አቅም ግንባታ ላይ ያተኮረ መሆኑንም አመልክተዋል።

በዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ገመዶ ዳሌ በበኩላቸው፤  ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለችውን የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራምና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ጋር የሚላመድና የሚያጣጣም  መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ለቀጣይ ሶስት ዓመታት የሚቆይ ነው ያሉት ሃላፊ፤ ለተግባራዊነቱ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

"በተለይ ሙቀት አማቂ ጋሶችን መጦ ለማስቀረት በተፈጥሮ ሀብት ልማትና እንክብካቤ፣ የድርቅና ጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ብሎም ይሄን መቋቋም የሚያስችል አቅም ለመገንባት ያለመ ፕሮጀክት ነው"ብለዋል።

 ከዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ የሚካሄድ ነው ያሉት ዶክተር ገመዶ።

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ዕቅዱን ማስፈፀም የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት እንዳለት ጠቅሰው፤ በዚህም በዘርፉ ያለውን ክፍተት ለመሙላትና ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችል ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም