በስርዓተ ምግብ ላይ የሚታየውን ክፍተት ለመቅረፍ ቅንጅታዊ አሰራርን መከተል እንደሚገባ ተገለፀ

80
ሀዋሳ ነሀሴ 10/2010 በስርዓተ ምግብ ላይ የሚታየውን ክፍተት በመቅረፍ ጤናማና አምራች ትውልድ ለመፍጠር ቅንጅታዊ አሰራርን መከተል እንደሚገባ የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡ “አላይቭ ኤንድ ትራይቭ'' የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በሃገሪቱ ስድስት ክልሎች በታዳጊና ጨቅላ ህጻናት አመጋገብ ላይ በሚጀምረው ፕሮግራም ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡ በውይይቱ ላይ የተገኙት የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብረሃም አላኖ እንደገለጹት የስርዓተ ምግብ ጉድለት ለህጻናትና እናቶች ጤና መታወክ ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ ክልሉ በሃገር ደረጃ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተጠቂ ከሆኑ ክልሎች በሶስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በዚህ ዘርፍ መስራታቸው ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡ “በስርዓተ ምግብ ላይ የሚታየውን ክፍተት በመቅረፍ ጤናማና አምራች ትውልድ ለመፍጠርም ቅንጅታዊ አሰራርን መከተል አስፈላጊ ነው'' ብለዋል፡፡ በክልሉ 44 ከመቶ የደረሰውን የመቀንጨር ችግር በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ማብቂያ 28 ከመቶ ለመቀነስ እቅድ ተይዞ እየተሰራ በመሆኑ የፕሮጀክቱ መጀመር እቅዱን ለማሳካት አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ እንደመንግስት የተፈጠሩ አደረጃጃቶች መኖራቸውን ጠቅሰው ተሞክሮዎችን በመቀመርና ክፍተቶችን በመለየት ውጤታማ ስራ ማከናወን እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ በአላይቭ ኤንድ ትራይቭ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ታደለ ቦጋለ በበኩላቸው ድርጅታቸው ላለፉት 10 ዓመታት በህጻናትና እናቶች አመጋጋብ ላይ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ በፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ በሃገሪቱ በታዳጊና ጨቅላ ህጻናት አመጋገብ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን የመለየት ስራ በደቡብ አማራ፣ ትግራይና ኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 295 ወረዳዎች ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡ በሁለተኛው ምእራፍ ደግሞ በሃገር ደረጃ በምግብ አቅርቦትና ማምረት ከፍተኛ ድርሻ እያለው መቀንጨር ጎልቶ በሚታይበት በአማራ ክልል 19 ወረዳዎች ውስጥ ባሉ 531 ቀበሌዎች ላይ መተግበሩን ተናግረዋል፡፡ በዚህም በሃገሪቱ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች በሆኑ ህፃናት ያለውን 38 በመቶ የመቀንጨር ምጣኔ በአጭር ጊዜ ወደ 22 በመቶ ማድረስ ተችሏል፡፡ በሃገር ደረጃ የተቀረጸው ብሄራዊ የስርዓተ ምግብ ፕሮግራምና በሰቆጣው ስምምነት መሰረት እ.ኤ.አ በ2030 የመቀንጨር ምጣኔውን ዜሮ ለማድረግ ለሚደረገው ርብርብ ከፍተኛ እገዛ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ በፕሮጀክቱ ሶስተኛ ምዕራፉም የተገኙ ተሞክሮዎችን በመቀመር በመላ ሃገሪቱ ስድስት ክልሎች እስከ 2015 ዓ.ም የሚከናወን ይሆናል፡፡ አማራ፣ደቡብ፣ትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ሱማሌና አፋር ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የሚሆንባቸው ክልሎች ሲሆኑ ከቢልና ሚንዳጌት ፋውንዴሽን 11 ነጥብ 4 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በጀት መመደቡን ገልጸዋል፡፡ አንድ ህጻን መቀንጨር ችግር ሲጋጥመው በእድሜው ሊኖረው የሚችለው የአእምሮና የአካል እድገት አይኖረውም ያሉት ደግሞ የስነ ምግብ ባለሙያዋ ዶክተር የውልሰው አበበ ናቸው፡፡ መቀንጨር ከእርግዝና ጊዜ ጀምሮ እንደሚያጋጥምና ጡት ማጥባትን ጨምሮ ተጨማሪ የተመጣጠነ ምግብ በሚያስፈልጋቸው የመጀመሪያዎች አንድ ሺህ ቀናት ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ በመድረኩ ላይ ከጤና፣ ከእርሻና ተፈጥሮ ሃብትና ከእንስሳትና ዓሳ ሃብት ዘርፍ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የተሳተፉ ሲሆን ለፕሮግራሙ ስኬታማነት ይጠቅማሉ ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም