አብዴፓ ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ከወሰኑ የአፋር ፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ገለፀ

71
ሰመራ ነሐሴ 10/2010 የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፖርቲ / አብዴፓ/  በውጭ አገራት ሲንቀሳቀሱ ከነበሩና ወደ አገራቸው ተመልሰው ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ከወሰኑ የአፋር ፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ፡፡ የአፋር ህዝብ መንፈሳዊ መሪ ወደ ሀገራቸው መመለስም ለክልሉ ልማትና ሰላም የላቀ ትርጉም ያለው መሆኑም ገልጿል፡፡ የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አሊ አብደላ በሰጡት መግለጫ  የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ይዘው በውጭ አገራት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የክልሉ ተወላጆች ወደ አገራቸውና ክልላቸው ገብተው ሰላማዊ ትግል እንዲያካሂዱ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በቅርቡ በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ ሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ደርጅቶች ወደ ሀገራቸው ገብተው ሰላማዊ ትግል እንዲያካሂዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባደረጉት ጥሪ መሠረት የተለያዩ የአፋር ፖለቲካ ደርጅቶች ወደ ሀገራቸው በመግባት ላይ መሆናቸውንም ገልፀዋል። የፖለቲካ ድርጅቶች በውጭ ሀገራት ተቀምጠው አንዱ ሌላውን እየከሰሰና እየወቀሰ ከመቀጠል  ይልቅ ወደ አገራቸው ተመልሰው ባላቸው ልምድና እውቀት ህዝባቸውን ለማገልገል ያሳለፉት ውሳኔ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህም ለአፋር ህዝብና መሪ ድርጅቱ አብዴፓ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር አብሮ ለማደግና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋግጥ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም አብዴፓ የአፋር ህዝብ ጉዳይ ያገባኛል ከሚሉና አማራጭ ካላቸው ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ተቀረርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይም የአፋር ህዝብ መንፈሳዊ መሪ ሱልጣን ሃንፈሪ አሊሚራህ ወደ አገራቸው መመለስ ለአፋር ህዝብ የበለጠ አንድነትና ሰላም  መጎልበት የጎላ ሚና እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡ ሱልጣን ሃንፈሪ አሊሚራህ  ያላቸውን ተሰሚነት ተጠቅመው መንግስት በጀመረው የልማትና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ዙሪያ ህብረተሰቡን በማነቃነቅ  የተጀመረው የህዳሴ ጉዞ ጫፍ እንዲደርስ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አብዴፓ/ በቀጣይ ከሱልጣን ሃንፈሪ አሊሚራህ ጋር ተቀራርቦ በመስራት የአፋርን ህዝብ ከድህነትና ኋቀርነት ለማውጣት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም