የአዲስ መንግስት መመስረት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር መሰረት የሚጣልበት ነው

187

መስከረም 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የሚካሄደው የአዲሱ መንግስት ምስረታ ከመደበኛው የፖለቲካ ሂደት ባሻገር አገሪቷን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር መሰረት የሚጣልበትና ሰፋፊ ተግባራት የሚከናወንበት መሆኑ ተጠቆመ።

የአገር ግንባታ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ከዛሬ በተጨማሪ የነገ የኢትዮጵያ አቅሞችን የሚመለከቱ መሆን እንዳለባቸውም ነው የተገለጸው።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት አዘጋጅነት የሚካሄደው አዲስ ወግ የውይይት መድረክ “በአዲስ መንፈስ አዲስ ውል – የመንግስት ምስረታ እና አገር ግንባታ” በሚል ርዕስ ዛሬ ተካሂዷል።

ውይይቱ በዋናነት አዲስ የሚመሰረተው መንግስት በሚያካሂዳቸው የአገረ መንግስት ግንባታ ስራዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር።

በመድረኩ ላይ የአገር ግንባታ ስራዎች፣ የአገር ደህንነት፣ ምጣኔ ሃብት ጉዳዮች እንዲሁም የሲቪል ሰርቪስ ስራዎችን በተመለከተ በተለያዩ ባለሙያዎች የውይይት መነሻ ፅሁፍ ቀርቧል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የማክሮ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አማካሪ ማሞ ምህረቱ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ልትፈታቸው የሚገቡ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የጸጥታ ችግሮች አሉባት።

ለአብነትም 60 ሚሊዮን የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ምንም ዓይነት የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደማያገኝ አንስተዋል።

በመሆኑም አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ኢትዮጵያን ካሉባት ውስብስብ ችግሮች የማሻገር ሃላፊነት እንደሚጣልበት ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የመንግስት ምስረታ ሂደቱ ከመደበኛው የፖለቲካ ሽግግር ባሻገር ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር መሰረት የሚጣልበት መሆኑን አብራርተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍስሃ ይታገሱ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ወንድማማችነት ላይ መሰረት ያደረገና አገራዊና ብሔራዊ ማንነትን ያጣጣመ የአገር ግንባታ ስራ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዝሃ-ማንነት ያላቸው አገሮች ላይ የሚነሱ የዴሞክራሲና ነጻነት ጥያቄዎች በወንድማማችነት እሴት ሊፈቱ እንደሚገባ አመላክተዋል።

የአገር ግንባታ ስራዎች ውጤታማ የሚሆኑት ቀጣይ አገር በሚረከበው ትውልድ ላይ ከወዲሁ በመስራት መሆኑንም ነው የጠቀሱት።

በመከላከያ ሠራዊት ግንባታ የጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ኮሎኔል ፍቅረየሱስ ከበደ፤ ጠንካራ የመከላከያ ሠራዊት መገንባት የጠንካራ አገረ መንግስት ግንባታ አካል መሆኑን ገልጸዋል።

ጠንካራ የመከላከያ ሠራዊት ከሚገነቡባቸው ቁልፍ ዘዴዎች አንዱ ተቋሙን ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ማድረግ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተግባር ላይ ያለው አዲሱ የሠራዊት ግንባታ ስትራቴጂ ይህን መሰረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

“ይህም ሙያውን በብቃት የሚተገብር ሠራዊት እንዲገነባ ያስችላል” ሲሉ ገልጸው፤ ሠራዊቱ ሁሉንም ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን በማሳተፍ መገንባቱን ገልጸዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ስብራቶች በዘላቂነት ለማቃለል ፖሊሲና ሰነዶች ተዘጋጅተው ወደ ትግበራ መገባታቸውን ያነሱት ደግሞ የፕላንና ልማት ኮሚሽነር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ናቸው።

አዲስ የሚመሰረተው መንግስት እነዚህ ተግባራትን በውጤታማነት በማስቀጠል ረገድ ከወዲሁ ዝግጁ መሆኑንም ነው ያነሱት።

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ገብረየሱስ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የአገረ መንግስት ግንባታ ላይ እንቅፋት ከሚሆኑ ጉዳዮች አንዱ በመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታየው ብልሹ አሰራር ነው።

ይህንን ብልሹ አሰራር በማቃለል ረገድ አዳዲስ አሰራሮች ተበጅተው ወደ ስራ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ለአብነትም ተሿሚዎችን ጨምሮ አገልግሎት ሰጪ አካላት የብቃት ውል ስምምነት ገብተው ወደ ስራ እንዲገቡ የሚያደርግ አሰራር እንደሚዘረጋ አውስተዋል።

ይህም የመንግስት ሰራተኛው “ምን ተሰጥቶት ምን አከናወነ የሚለውን ለመቆጣጠር ያስችላል” ብለዋል።