በዲላ ዙሪያ ወረዳ ከ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነባ ጤና ጣቢያ ለአገልግሎት በቃ

142

ዲላ፤ መስከረም 19/2014 (ኢዜአ) በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ ከ5 ሚሊዮን 5 መቶ ሽህ ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነባ የወቸማ ጤና ጣቢያ ተመርቆ ለአገልግሎት በቃ።

ጤና ጣቢያው በ7 ቀበሌዎች ለሚገኙ ከ25 ሺህ በላይ ህዝብ አገልግሎት እንደሚሰጥ በምረቃው ስነ-ሰርዓት ላይ ተገልጿል።

የወረዳው ጤና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አንዱአለም ማሞ እንዳሉት፤ ጤና ጣቢያው በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃት ተችሏል።

ለግንባታውም ከ5 ሚሊዮን 5 መቶ ሺህ ብር በላይ ወጪ መደረጉን አመልክተው፤ የወሊድና እናቶች ማቆያን ጨምሮ 12 የህክምና አገልግሎት የሚሰጥባቸው ክፍሎችን ማካተቱን  ገልጸዋል።

በወሊድ ምክንያት አንድም እናት እንዳትሞት በተያዘው ዕቅድ መሰረት የወሊድ አገልግሎትን በአካባቢው ለሚገኙ እናቶች በቅርበት ለመስጠት ያስችላል ያሉት ደግሞ  የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ያዕቆብ ጤኮ ናቸው።

ይህንን ጥረት ለማጠናከር ለጤና ጣቢያው ለእናቶች የወሊድ አገልግሎት ብቻ የሚሆን አንቡላስ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽፈራው ቦጋለ በበኩላቸው፤ የወቸማ ጤና ጣቢያ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱ የእናቶችንና ህጻናትን ጤና ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

ጤና ተቋሙ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ እንዲገባ የህክምና ግብዓቶች በማሟላቱ ረገድ የዞኑ አስተዳደር የበኩሉን እንደሚወጣ አሰታውቀዋል።

በምረቃው ስነ-ስርዓት የዞንና ወረዳ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ነዋሪዎችና የደረጃው የሚገኙ ጤናው ዘርፍ ሃላፊዎች መገኘታቸውን የኢዜአ ሪፖርተር ከሥፍራው ዘግቧል።