የሚመሰረተው መንግስት ሀገሪቱን ከገጠማት ችግር በማውጣት ጠንከራ ኢኮኖሚ መገንባት ይጠበቅበታል

170

ባህር ዳር ፤ መስከረም 19/2014 (ኢዜአ) አዲስ የሚመሰረተው መንግስት አካታች የፖለቲካ ምህዳር ከማዳበር ባለፈ ሀገሪቱን ከገጠማት ወቅታዊ ችግር በማውጣት ጠንከራ ኢኮኖሚ መገንባት እንደሚጠበቅበት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ  በቅርቡ አዲስ በሚመሰረተው መንግስትና ቀጣይ ሥራዎቹን አስመልክተው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት መንግስት የሀገሪቱን የውጭ ግንኙነት ማጠናከር ላይ አበክሮ መስራት እንዳለበትም ገልጸዋል።

የአማራ ብሔራዊን ቅናቄ (አብን) የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጣሂር መሃመድ እንዳሉት፤በሀገሪቱ አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ከወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ አንጻር ከባድ ሃላፊነቶች አሉበት።

ሃላፊነቱን ለመወጣትም ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ብቻ ሳይሆን በልዩ ለዩ የሙያ ዘርፎች በመሰማራት አገራቸውንና ህዝባቸውን በቅንነት ለማገልገል እውቀት ያላቸው ግለሰቦችንም አካቶ መስራት እንዳለበት ነው ያመለከቱት።

አካታች የፖለቲካ ስርዓት መዘርጋት ለዘላቂ እድገት ከሚኖረው ፋይዳ በተጨማሪ ሀገር ካለችበት ችግር  እንድትወጣ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

"የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ጫናን በድል መወጣት የሚቻለውም በያገባኛል ስሜት ለሀገር ተባብሮና ተጋግዞ መስራት ሲቻል ነው" ብለው አቶ ጣሂር።

የኢትዮጵያን ውስብስብ ችግር ለመፍታትና ለሀገር ሁለንተናዊ ለውጥ አዲስ የሚመሰረተው መንግስት አካታችና አሳታፊ የፖለቲካ ምህዳርን ቢያዳብር  የተሻለ መሆኑንም አስረድተዋል።

ለዜጎች የሥራ እድል መፍጠር፣ ሀገሪቱን ማሻገር የሚችል ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባትና ከዚህ ቀደም ተሞክረው ውጤታማ ያልሆኑ ፖሊሲዎችን መልሶ መከለስ እንዳለበትም ነው ያመለከቱት።

"ከሦስት ዓመት በፊት የመጣው ሀገራዊ ለውጥ  በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል የተገኘ ነው" ያሉት ደግሞ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የምዕራብ ጎጃም ዞን ሰብሳቢ ፣ የባህር ዳርና አካባቢው አስተባባሪ አቶ መላኩ በላይ ናቸው።

በኢትዮጵያ ህዝብ ትግል የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል፣ በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ የገጠማትን የውስጥና የውጭ ጫና ለመቋቋም የመንግስት ምስረታው ሁሉን ያካተተና አቅምን መሰረት ያደረገ መሆን እንዳለበት ነው ያመለከቱት።

"አዲስ በሚመሰረተው መንግስት አሳታፊ የሆነ ሥርዓት ለመዘርጋት እየታየ ያለው ፍላጎት የሚበረታታ  ነው" ያሉት ደግሞ የአማራ ዴሞክራሲ ሀይል ንቅናቄ (አዴሃን) ሊቀመንበር አቶ ተስፋሁን አለምነህ ናቸው።

አዲስ የሚመሰረተው መንግስት በተለይ የውጭ ዲፕሎማሲው እውቀትና ብቃት ባላቸውና እውነተኛ የሀገር ስሜት በሚሰማቸው ግለሰቦች እንዲመራ የማድረግ ሥራ ትኩረትሊሰጠው እንደሚገባም አስተያየት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም