የአልኮል መጠጥ፣ ትምባሆና ሌሎች አደንዛዥ እጾችን መጠቀም ለልብ ህመም ዋነኛ ምክንያት እየሆኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአልኮል መጠጥ፣ ትምባሆና ሌሎች አደንዛዥ እጾችን መጠቀም ለልብ ህመም ዋነኛ ምክንያት እየሆኑ ነው
አዲስ አበባ መስከረም 19/2014 (ኢዜአ ) የአልኮል መጠጥ፣ ትምባሆና ሌሎች አደንዛዥ እጾችን መጠቀም ለልብ ህመም ዋነኛ ምክንያት እየሆኑ ነው።
በኢትዮጵያም በአሁኑ ወቅት 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎች የልብ ታማሚዎች ሆነዋል።
የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ማዕከል የዓለም የልብ ቀንን አስመልክቶ ለሦስት ቀናት የሚደረግ ነጻ የቅድመ ምርመራ አገልግሎት፣ የደም ልገሳ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ-ግብር አስጀምሯል።
የማዕከሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ህሩይ አሊ፤ በርካታ ዜጎች ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ሳቢያ ከፍተኛ የጤና ቀውስ ሲገጥማቸው ይስተዋላል ብለዋል።
እንደ ካንሰር፣ ልብና ስኳር የመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በህብረተሰብ ጤና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደሩ ያሉ በሽታዎች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
በተለይም የልብ ህመም በአሁኑ ወቅት አሳሳቢ እየሆኑ ከመጡ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ከበሽታው አሳሳቢነት እንዲሁም በአገሪቱ ያለው የልብ ህክምና አገልግሎት ተደራሽነት አናሳ ከመሆኑ አንጻር ማህበረሰቡ ቅድመ መከላከል እና ጤናማ የህይወት ዘይቤን መከተል ላይ ትኩረት መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ወንድሙ፤ የልብ ህመም በዓለም ላይ ገዳይ ከሚባሉ እና የሰዎችን ህይወት በእጅጉ ከሚቀጥፉ አሳሳቢ በሽታዎች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለዚህም በተለይ ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ሥርዓት፣ የአልኮል መጠጥ፣ ትምባሆና ሌሎች አደንዛዥ እጾችን መጠቀም ለበሽታው መባባስ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
የአካል እንቅስቃሴን አለማድረግ በበሽታው የመጠቃት እድልን እንደሚጨምር ገልጸው በሽታው በሰዎች ጤና ላይ ከሚያስከትለው ቀውስ አኳያ ልዩ ትኩረት ይሻል ብለዋል።
ማህበረሰቡ ጤናውን ከመጠበቅ ጎን ለጎን የደም ልገሳ በማድረግ በተለያየ ምክንያት በደም እጥረት ህይወታቸውን ለሚያጡ ዜጎች እንዲደርስም ጥሪ አቅርበዋል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዓለም ላይ በየዓመቱ 15 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሰዎች በልብ ህመም እና ከልብ ህመም ጋር ተያይዘው በሚከሰቱ የጤና እክሎች ምክንያት ህይወታቸው ያልፋል።
በኢትዮጵያም በአሁኑ ወቅት 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎች የልብ ታማሚዎች መሆናቸውንም መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የደረት ህመም፣ ትንፋሽ ማጠር፣ ማስመለስ /ማቅለሽለሽ/፣ በድንገት ማላብና አቅም ማጣት የድንገተኛ የልብ ህመም ምልክቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ አስቸኳይ ህክምና ማድረግ ያስፈልጋል ተብሏል።
የዓለም የልብ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1999 ጀምሮ በየዓመቱ የሚከበር ሲሆን፤ ይህም የልብ ህመም አሳሳቢነት እና ግንዛቤ ለመፍጠር ታስቦ የሚደረግ ነው።