በመሬት፣ በቤት ልማት እና በስራ ዕድል ፈጠራ ላይ በመዲናዋ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ እናደርጋለን

145

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19/2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ በመሬት፣ በቤት ልማት እና በስራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ እናደርጋለን ሲሉ አዲስ የተሾሙ የስራ ሃላፊዎች ተናገሩ።

የአዲሰ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በከንቲባ አዳነች አቤቤ የቀረበለትን የካቢኔ ሹመት በማጽደቅ ትላንት ተመስርቷል።

ከአዳዲስ ተሿሚዎች መካከል ኢዜአ የቤቶች ልማትና አስተዳደር፣ የስራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት እንዲሁም የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮዎች ሃላፊዎችን አነጋግሯል።

ምክትል ከንቲባና የስራ፣ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ ሆነው የተሾሙት አቶ ጃንጥራር አባይ ህዝብ የሰጣቸውን ሃላፊነት በብቃት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በስራ እድል ፈጠራ፣ በኢንተርፕራይዝ እንዲሁም በኢንዱስትሪ ልማት የሚታቀዱ እቅዶችን ከህዝብ ጋር ተግባቦት በመፍጠር እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የቤቶች ልማት ቢሮ ሃላፊ ያስሚን ውሃብረቢ፤ በከተማዋ የቤቶች ልማት ላይ የሚስተዋለውን ክፍተት ለመሙላት የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የመኖሪያ ቤት እጥረት ችግርን ለመፍታት መንግስት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ከህዝብ ቁጥር አጻር በመኖሪያ ቤት ጉዳይ ሰፊ ክፍተት መኖሩን ጠቅሰው በመንግስትና የግል አጋርነት የተጀመሩ ስራዎችን በማስፋት ሌሎች አማራጮችን በመተግባር የቤት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት እንሰራለን ብለዋል።

የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ሆነው የተሾሙት አቶ ጀማል አልዬ፤ በዘርፉ የአደረጃጀት፣ አሰራርና ሌሎች ማስተካከያዎችን በማድረግ ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት እንሰራለን ብለዋል።

ለሚተገበሩ አዳዲስ አሰራችን የከተማዋ ነዋሪዎች ለውጤታማነቱ እገዛና ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በየሴክተሩ አዲስ የተሾሙት አመራሮች  ህዝብን በቁርጠኝነት ለማገልገል መዘጋጀት አለባቸው ብለዋል ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ።

ምክር ቤቱ ከብልጽግና ፓርቲ አባላት በተጨማሪ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች መካከልም ሹመት መስጠቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም