በአዲሱ ዓመት ዋዜማ የተለያዩ ከተማ አቀፍ የበጎ አድራጎት ተግባራት ይከናወናሉ- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር

61
አዲስ አበባ ነሓሴ 10/2010 መጪውን አዲስ ዓመት 'የአዲስ ተስፋ ቀመር' በሚል የተለያዩ በጎ አድራጎት ተግባራትን በማከናወን እንደሚቀበል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ። በዚህም ከተማ አስተዳድሩ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ወጣቶችንና የኪነ ጥበብ ቤተሰቦችን በማስተባበር 114 የአቅመ ደካማ ቤቶችን ለማደስና 96 የቆሸሹ ስፍራዎችን ደግሞ ለማጽዳት ለይቷል። የከተማው ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ከተማ አስተዳደሩ መጪውን አዲስ ዓመት ለመቀበል ያለውን አገራዊ ለውጥና መነሳሳት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በከተማዋ ውስጥ የተለያዩ ማህበራዊ በጎ አድራጎቶችን ያከናውናል። 'ምን እናድርግ፣ ምን እናግዝ ' የሚል የመነሳሳት መንፈስ ያዳበሩ ወጣቶች እንዳሉ የጠቆሙት ምክትል ከንቲባዋ፤ የአዲስ ተስፋ መርሃ ግብርም 'ጥላቻን መቀነስ፣ያለንን ማካፈል፣ ይቅርታን ማባዛትና በፍቅር መደመር' በሚል ቀመር የሚከናወን ነው ብለዋል። በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችንና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ያካተተው መርሃ ግብሩ፤  እያንዳንዱ ዜጋ  ያለውን አገራዊ የለውጥ ፍላጎትና መነሳሳት ወደተግባር እንዲለውጥና በአርዓያነት እንዲወስደው ያለመ መሆኑንም አንስተዋል። በዚህም ከዛሬ ጀምሮ እስከ ነሐሴ 24 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ የአቅመ ደካማ ሰዎችን ቤቶች ለማደስና ለአቅመ ደካሞች በልዩ ልዩ መንገዶች እገዛ የማድረግ ተግባር የሚከናወን ሲሆን ለዚህም በከተማዋ 114 ወረዳዎች ውስጥ በእያንዳንዱ ወረዳ አንድ ቤት ይታደሳል። አዲስ አበባ ስሟን የሚመጥን ገጽታና ጽዳት እንደሚያስፈልጋት የገለጹት ወይዘሮ ዳግማዊት፤ በዚህ የመደመር ዘመን 96 እጅግ የቆሸሹ ስፍራዎችን ታዋቂ ግለሰቦች፣ አርቲስቶችና ወጣቶች በተሳተፉበት ከነሐሴ 25 ጀምሮ የጽዳት ዘመቻ እንደሚከናወን ተናግረዋል። በሌላ በኩል በመዲናዋ በኑሯቸው የተቸገሩ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉ በማንሳት፤  'የእናት አገሬ ስጦታ' በሚል እነዚህ ዜጎችን በመርዳትና ሕይወታቸው እንዲቀየር የሚያስችሉ መድረኮች ተፈጥረው የበጎ አድራጎት ተግባራት ይከናወናሉ። ከ30 ሺህ በላይ የመዲናዋ ህጻናት ተማሪዎች የትምህርት አልባሳትና ቁሳቁሳቸውን ማሟላት እንደማይችሉ በጥናት መለየቱን ለአብነት አንስተው፤ ማንኛውም ድጋፍ ማድረግ የሚችል አካል ድጋፍ እንዲያደርግም ማድረግ አንደኛው የአዲስ ተስፋ ቀመር አካል ነው ብለዋል። "አገር ማለት ሰዎችና የነገ አገር ተረካቢ ህጻናት ናቸው" ያሉት ምክትል ከንቲባዋ በመዲናችን ከ7 ሺህ በላይ ምግብ የሚቸገሩ ህጻናት ተማሪዎችን ህይወት የሚቀይር ስራም ለማከናወን ታቅዷል ነው ያሉት። ከሁለት ቀን በኋላ ነሐሴ 12 ቀን 2010 ዓ.ም በእንጦጦ ማርያም አካባቢ የተለያዩ የህብረተሰብ ከፍሎች የሚሳተፉበት የችግኝ ተከላ ፕሮግራም እንደሚከናወንም ተናግረዋል። አዲሱን ዓመት በአንድነትና በጋራ ድባብ ለመቀበል በአዲስ ዓመት ዋዜማ መግባባትን፣ አንድነትንና ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎሉ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶች በጳጉሜ መጨረሻ ላይ እንደሚካሄዱ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም