በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ተለይተው ነዋሪዎች የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ እንሰራለን

178

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18/2014 (ኢዜአ) በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ተለይተው ነዋሪዎች የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ እንሰራለን ሲሉ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት ተናገሩ።

''አዲስ ምዕራፍ'' በሚል ሶስተኛው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ዛሬ በይፋ ተመስርቷል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ሴት የምክር ቤት አባላት በከተማዋ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች መኖራቸውን አንስተዋል።

በአንድ ጀንበር ችግሮችን መፍታት አዳጋች ቢሆንም ነዋሪው ተደጋጋሚ ቅሬታ የሚያነሳባቸውን የአገልግሎት ዘርፎች በመለየት የተሻለ አሰራር እንዲፈጠር በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።

በተለይም በአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ላይ ያለውን አሰራር ማሻሻል የምክር ቤት አባላቱ ተቀዳሚ ተግባር ይሆናል ነው ያሉት።

ከምክር ቤት አባላት መካከል ውዳላት ገዳሙ፤ ህዝብ አምኖ የሰጠውን ሃላፊነትን ተቀብሎ መፈጸም ለነገ የማይባል ተግባር ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ እና ሌሎችም ዘርፎች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በሂደት ምላሽ እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ለአገሪቷ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሰረት ጥሎ ለማለፍ ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

ሌላዋ የምክር ቤት አባል ሰላማዊት ካሳ፤ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ከተለያዩ ሙያና የትምህርት ደረጃ የተዋቀረ እንደመሆኑ ከነዋሪዎች ለሚነሱ የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች በቅንጅት ለመፍታት ዕድል ይሰጣል ብለዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በምርጫ ቅስቀሳ ጊዜ ከህብረተሰቡ ጋር በቅርብ ለመተዋወቅ ዕድል የፈጠረላቸው መሆኑንም ነው የተናገሩት።

አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ ለማድረግና የነዋሪዎቿን መሰረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ ህዝብ የጣለባቸውን ሃላፊነታቸውን በትጋት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን በመግለጽ ።

ከምክር ቤት አባላት መካከል ዶክተር እመቤት ገዛሃኝ እና ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ፤ ህዝብ ቅሬታ የሚያነሳባቸው አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ያለውን መሰረታዊ የአሰራር ችግር በመለየት ለመፍትሄው እንደሚተጉ ነው የተናገሩት።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፤ ዛሬ ከተሾሙ በኋላ ባደረጉት ንግግር የከተማዋን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት አባላት 138 ሲሆኑ የአስተዳደሩን ስራ አስፈፃሚዎች የስራ ክንውን የመከታተልና ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ሃላፊነት እንዳለባቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም