ያለፈው ሣምንት በኮቪድ-19 ከፍተኛው የሞት መጠን የተመዘገበበት ነው

147

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18 /2014 (ኢዜአ) የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ጀምሮ ባለፈው ሣምንት የተመዘገበው የሞት መጠን ከፍተኛ መሆኑን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
የኢንስቲቲዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጽጌረዳ ክፍሌ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አዲሱ የኮቪድ-19 ዝርያ ዴልታ ቫይረስ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጨ ነው ብለዋል።

ከመስከረም 10 እስከ 16 ቀን 2014 በአገር አቀፍ ደረጃ ከተመረመሩ 57 ሺህ 940 ሰዎች መካከል 8 ሺህ 753 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን የመያዝ ምጣኔውም 15 በመቶ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሎችም በተመሳሳይ የመያዝ ምጣኔው ከአገር አቀፍ የመያዝ ምጣኔ ከፍ ብሎ መታየቱን ጠቁመዋል።

በዚሁ ሣምንት በአገር አቀፍ ደረጃ በኮቪድ-19 ሳቢያ የ271 ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን ከነዚህም 175ቱ ከአዲስ አበባ ናቸው።

እንደ ዶክተር ጽጌረዳ ገለጻ ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ከተከሰተ ጀምሮ ከፍተኛ የሞት መጠን የተመዘገበበት ሣምንት ነው።

በተመሳሳይ በዚሁ ሣምንት ከ798 በላይ ታማሚዎች ወደ ጽኑ ሕክምና ማዕከል ገብተው ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባና በአንዳንድ የክልል ከተሞች የታካሚዎች ቁጥር ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ የጽኑ ሕክምና ክፍሎች ሞልተው ታካሚዎች ለከፍተኛ ችግር እየተጋለጡ ነውም ብለዋል።

ይህ የመያዝ፣ የሞት እና የጽኑ ሕሙማን ቁጥር መጨመር የአዲሱ ኮቪድ-19 ዴልታ ቫይረስ ስርጭት ከፍተኛ መሆኑን እንደሚያሳይ ጠቁመዋል።

የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶች ተግባራዊ አለመደረጋቸው እና የክትባት ሽፋን ዝቅተኛ መሆንም ለስርጭቱ መስፋፋት በምክንያት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ በተመረጡ 14 ከተሞች የመከላከያ መንገዶች አተገባበርን አስመለክቶ በተደረገ ጥናት ትግበራው ዝቅተኛ መሆኑንና በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ መዘናጋት መኖሩን ማወቅ ተችሏል ብለዋል።

ለወረርሽኙ ፖለቲካዊ አንድምታ መስጠት፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ዓርአያ ሆነው አለመገኘት፣ በየደረጃው የተዋቀሩ ግብረ ሀይሎች መመሪያ የማስፈጸም ተሳተፎ እያነሰ መምጣት ኅብረተሰቡ የመከላከያ መንገዶችን እንዳይተገብር ምክንያቶች ሆነዋል ነው ያሉት።

ኅብረተሰቡ አሁንም ወረርሽኙ የሚያስከትላቸውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች በመገንዘብ ያለመሰልቸት የመከላከያ መንገዶችን እንዲተገብርም አሳስበዋል።

ሕይወታቸው ካለፈ መካከል አብዛኞቹ ያልተከተቡ መሆናቸውን የገለጹት ዶክተር ጽጌረዳ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች በጤና ተቋማት ሄደው እንዲከተቡም አስገንዝበዋል።

መገናኛ ብዙሀን፣ የመንግስትና የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና ሀላፊነት የተጣለበት ግብረ ሀይል ለወረርሽኙ ትኩረት በመስጠት የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።