በትግራይ ደቡባዊ ዞን ከ19 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በዘመቻ ተተከለ

56
ማይጨው ነሐሴ 10/2010 በትግራይ ደቡባዊ ዞን በዘንድሮው ክረምት ከ19 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በዘመቻ መተከሉን የዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡ በመምሪያው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ አቻምየለህ አሰፋ ለኢዜአ  እንደገለጹት ከሐምሌ አጋማሽ ጀምሮ በተካሄደው ዘመቻ ችግኙ የተተከለው በክረምት ወቅት ለመትከል ከተዘጋጀው 27 ሚሊዮን ችግኝ ውስጥ ነው፡፡ ችግኙ በዞኑ አምስት ወረዳዎች 11 ሺህ ሄክታር መሬት በሚሸፍኑ 174 ተፋሰሶች ላይ መተከሉን ገልፀዋል፡፡ ቀሪውን 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል ስራ አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን አቶ አቻምየለህ ተናግረዋል፡፡ በተከላ ስራው በ13 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡ ከአርሶ አደሩ በተጨማሪ በሀገር መከላከያ ሚኒስትር የሰሜን ዕዝ  ችግኝ ለማጓጓዝ የሚያግዝ የተሽከርካሪ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ የተተከለው ችግኝ እንዲፀድቅም አርሶአደሮች በበጋ ወቅት ውሀ ለማጠጣትና ከእንስሳትና ከሰው ንክኪ ከልለው ለመንከባከብ አደረጃጀት መፈጠራቸውን የቡድን መሪው ተናግረዋል፡፡ የእንዳመኾኒ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር  አለሙ ታደሰ ባለፉት ዓመታት የተካሄደው የችግኝ ተከላ ተራቁተው የነበረው የአካባቢያቸው ልምላሜ በማገገሙ በየዓመቱ በሚካሄደው የችግኝ ተከላ ስራ ያለማንም ቀስቃሽ በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ባለፈው ዓመት በዞኑ አምስት ወረዳዎች ከተተከለው 34 ሚሊዮን ችግኝ ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆን መፅደቁን ከዞኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም