ቀጥታ፡

አሸባሪውን ቡድን ከአማራ ክልል ጠራርገን በማስወጣት ደስታችንን ሙሉ እናደርጋለን - የአፋር ወጣቶች

ደሴ፤ መስከረም 17/2014(ኢዜአ) ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን ተሰለፈን አሸባሪውን የህወሃት ወራሪ ቡድን ከአማራ ክልል ጠራርገን በማስወጣት ደስታችንን ሙሉ እናደርጋለን ሲሉ በአፋር የጭፍራ ወረዳ ወጣቶች አስታወቁ።

ከወረዳው ወጣቶች መካከል የታአቦና ገሪሮ ቀበሌ ነዋሪ  አብዱ እንድሪስ ለኢዜአ እንዳለው ፤  አሸባሪው የህወሃት ቡድን ከሰው ያልተፈጠረ፤ ጨካኝ ለመኖር እድል ሊሰጠው የማይገባ የወንበዴ ስብስብ ነው፡፡

ቡድኑ ከጠላቶቻችን ጋር ወግኖ ኢትዮጵያን ለማፍረስ አፋርና አማራ ክልልን በመውረር በህዝብ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ከፍተኛ  ግፍ ፈጽሟል።

የአፋር ህዝብ ከመከላከያና  ሌሎች የፀጥታ አባላት ጋር ተቀናጅቶ አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ከክልሉ ሙሉ በሙሉ ማስወጣት መቻሉን ተናግሯል፡፡

እኛም በእዋና በወረባቦ ወረዳ በኩል ወደ ጭፍራ ለመግባት የቋመጠውን ወራሪ ቡድን መውጫ ቀዳዳ በማሳጣት በገባበት ደምስሰን በመቅበር እንዳይወጣ አድርገነዋል ብሏል ወጣት  አብዱ ፡፡

ሆኖም አሸባሪው  ከአፋር መውጣቱ ቢያስደስተንም ከሚያጎራብተን የአማራ ክልል ሙሉ በሙሉ ተጠራርጎ ካልወጣ ደስታችን ሙሉ አይሆንም ያለው ወጣቱ ፤ ከሰራዊቱ ጋር ተሰልፈው እስከ መጨረሻው ለመቅበር ቆርጠን መነሳቸውን ገልጿል።

ሌላው የጭፍራ ከተማ  ወጣት አማን ወግሪስ በበኩሉ፤ አሸባሪውን ህወሃትና መሰሎቹን እንዳይነሱ አድርጎ መቅበርና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማስቀጠል ከሁላችንም ይጠበቃል ብሏል፡፡

የሽብር ቡድኑ  ድንገት ቢወረንም በተባበረ ክንድ ቀጥቅጠን ወደ መጠባት መመለስ ችለናል ነው ያለው።

ነገር ግን በአማራ ክልል ህዝብ ላይ አሁንም ግፍ እየፈጸመ በመሆኑ በተደራጀ አግባብ ቀብረን ደስታችንን ሙሉ ለማድረግ እስከ ህይወት መስዋትነት ለመክፈል በቅንጅት እየሰራን ነው ሲል ወጣት አማን ተናግራል።

 የአፋር ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር አንድነቱን ጠብቆ በአባቶቻችን ደምና አጥንት የተከበረች ሀገርን በዘላቂነት ሉአላዊነቷንና  ሰላሟን ለመጠበቅ የማይከፈል መስዋትነት አይኖርም ብሏል፡፡

በአፋር ክልል ፈንቱ ረሱና በአማራ ክልል ወረባቦና ሀብሩ አካባቢዎች በኩል ሊዘርፍ የመጣውን ወራሪ ጠላት ለአንድ ወር ያህል ጫካ ውስጥ ሲዋጋ መቆየቱን አስታውሶ ፤ በቅንጅት ባደረጉት ርብርብ ጭፍራ ሳይገባ ባለበት እንዲቀበር መደረጉን አመልክቷል።

አሁንም ይህን ሀገር ሻጭና ዘራፊ ቡድን  ዋሻ ሳይሆን ጉድጓዳ ካላስገባነው ረፍት የለንም  ነው ያለው ወጣቱ።

''አሸባሪው የህወሃት ቡድን በገባባቸው የአፋርና የአማራ ክልል አካባቢዎች በህዝብ ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ ግፍና በደል የምንበቀለው  ዳግም ስጋት በማይሆኑ መልኩ መቅበር ስንችል ነው'' ያለው ደግሞ ወጣት አህመድ አሊ ነው፡፡

በሰሜን ወሎ ያለባቸው አካባቢዎች መቀበሪያው እንዲሆን ከመከላከያ፣ ከልዩ ኃይልና ከአማራ ክልል ፋኖና ወጣቶች ጋር በቅንጅት እያሰስን መድረሻ እያሳጣነው ነው ብሏል፡፡

የጭፍራ ወረዳ የስራ አመራር የሆኑት አቶ ወግሪስ ሀፋ በበኩላቸው፤ ወጣቶቹ  ከሰራዊቱና ከአጎራባች የአማራ ክልል እኩዮቻቸው  ጋር በማቀናጀት የሽብር ቡድኑን በመፋለም  ውጤት ማስገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከክልላችን ሙሉ በሙሉ ቢወጣም በጎረቤት ወንድም እህቶቻችን ላይ አሁንም ግፍ እየፈጸመ በመሆኑ ቡድኑን ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበር አመራሩም ከሚመለከተው አካል ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም