ቀጥታ፡

"ለኢትዮጵያ ህልውና ሁሌም ዝግጁ ነን፤ ተቋማዊ ግንባታችንም ይቀጥላል"

መስከረም 17/ 2014(ኢዜአ) "ለኢትዮጵያ ክብርና ህልውና ሁሌም ዝግጁ ነን፤ ተቋማዊ ግንባታችንም ይቀጥላል" ሲሉ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ይልማ መርዳሳ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ አየር ሃይል የቆይታ ጊዜያቸውን ላጠናቀቁ እና የላቀ የስራ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አመራርና አባላት የማእረግ እድገት ሰጥቷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ አየር ሃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ይልማ መርዳሳ፤ ባለፉት ሶስት አመታት ኢትዮጵያን የሚመጥን የአየር ሃይል ለመገንባት ብዙ መሰራቱን ተናግረዋል።

እስካሁን በተሰራው ስራ የሚታይ ለውጥ በመምጣቱ በሕግ ማስከበር ዘመቻው አየር ሃይሉ ከፍተኛ የግዳጅ አፈፃፀም አስመዝግቧል ብለዋል።

በዚህ ሂደት የአየር ሃይል አባላት ጀግንነትና የመፈፀም ብቃት የላቀ እንደነበርም ጠቅሰዋል።

ሜጀር ጀነራል ይልማ በመልእክታቸው "ለኢትዮጵያ ክብርና ህልውና ሁሌም ዝግጁ ነን፤ ተቋማዊ ግንባታችንም ይቀጥላል" ብለዋል።

የአየር ሃይሉ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ያስከብራል፤ የተቋም ልማትና ግንባታውንም ይቀጥላል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ የተነሳው የመንደር ሽፍታም እርምጃ ይወሰድበታል ብለዋል።

የአየር ሃይል ምክትል አዛዥ ለሰው ሃይል ብርጋዴር ጀነራል ይታያል ገላው፤ የአየር ሃይል አባላት ለኢትዮጵያ ትልቅ ሃላፊነይ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።

''ኢትዮጵያ ትልቅ ፈተና ውስጥ ሆና ይህን ሃላፊነት መሸከም ትልቅ እድል ነው'' ያሉት ደግሞ የማዕረግ ሹመት ያገኙ ከፍተኛ መኮንኖችና መስመራዊ መኮንኖች ናቸው።

ከመቼውም ጊዜ በላይ ለአገራቸው ሉአላዊነት መከበር የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በተለይም አሁን ላይ የውስጥ ጠላት የሆኑትን አሸባሪዎቹን ሸኔ እና ህወሃት ለማጥፋት ዝግጁ ነን ብለዋል።

የማዕረጉ እድገቱ የተሰጣቸው ከፍተኛ መኮንኖች፣ መስመራዊ መኮንኖችና ባለሌላ ማዕረግተኞች ሲሆኑ በድምሩ 511 ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም