ቀጥታ፡

ሰልጣኝ ወጣቶች እየሰጡ ያለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለብሔራዊ መግባባት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል

ጅማ፤ መስከረም 17/ 2014(ኢዜአ) የሠላም ሚኒስቴር ብሔራዊ የበጎ ፍቃድ ሰልጣኝ ወጣቶች ለህብረተሰቡ እየሰጡ ያለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለብሔራዊ መግባባት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ተገለጸ።
የሠላም ሚኒስቴር ብሔራዊ በጎ ፈቃድ ሰልጣኝ ወጣቶች  የመስቀልና ደመራ በዓልን ምክንያት በማድረግ  በጅማ ከተማ የጎዳና ተዳዳሪዎችን የመርዳትና የፅዳት ዘመቻ አካሂደዋል። 

ወጣቶቹ ከከፍተኛው የትምህርት ተቋማት ተመርቀው ከተለያዩ የሀገሪቱ  አካባቢዎች የመጡ ሲሆን፤  ሚኒስቴሩ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በሀገር ግንባታ ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር፣ በስራ እድል ፈጠራና ከወጣቱ ለሀገር እድገት ተጠባቂ ተግባራትና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ  እያሰለጠናቸው ይገኛል።

በሚኒስቴሩ ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ ልማት አገልግሎት ስልጠና አስተባባሪ ወይዘሮ ትዕግስት ኃይለማሪያም  በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ወጣቶቹ ከአካባቢያቸው ውጭ ላሉ ወገኖች እየሰጡ የሚገኙት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አርአያነት ያለውና ለብሔራዊ መግባባት ወሳኝ ሚና የሚኖረው ነው።

ሰልጣኞች የአብሮነት እሴትን ለማጎልበት ለማህበረሰቡ አርያነት ያላቸው የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ላይ እየተሳተፉ መሆኑን አስረድተዋል።

የጎዳና ተዳዳሪ ወገኖችን ፀጉር በመላጨት፣ ገላቸውን በማጠብ፣ አልባሳት አዋጥተው በማልበስ፣ ደም በመለገስና መሰል በጎ ተግባር እየፈጸሙ እንደሚገኙ አስተባባሪዋ ገልጸዋል።

ከሰልጣኞቹ መካከል ወጣት ነኢማ ነጃ  "ስልጠናውን ከጀመርኩ በኋላ ለሰዎች መልካም ማድረግ የሚሰጠውን የህሊና እርካታ ተረድቻለው" ብላለች።

“እኛ በቻልነው ሁሉ ህብረተሰባችንን ለማገዝ እንሰራለን፣ እገዛ የሚያስፈልጋቸውንም  ባለን አቅም እናግዛለን”  ነው ያለችው።

ሰልጣኝ ተሰማ ጫካ በበኩሉ፤  በርካታ በጎ ተግባራትን በመስራት ላይ እንደሚገኙ ገልጾ፤ የጽዳት ዘመቻ እናካሄዳለን፣ የጎዳና ተዳዳሪ ወገኖችንም ገላ እናጥባለን፣ እናለብሳለን ፤ ደም እንለግሳለን” ብሏል።

ወገንን ማገልገል የሚሰጠውን ደስታ ተረድተውና  መልካምነትን ተምረው ለማህበረሰባቸው የቻሉትን እያደረጉ መሆኑን ወጣቶች ገልጸዋል፡፡

በጅማ ከተማ  በተካሄደው የጎዳና ተዳዳሪዎችን የመርዳትና የፅዳት ዘመቻ ስራ ላይ ከ2ሺህ በላይ  የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰልጣኝ ወጣቶች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም