ቀጥታ፡

ከ30 ዓመት በኋላ ወደ ትውልድ አገሬ ስመለስ መስቀልን ከነክብሩ አገኘሁት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 17/2014 (ኢዜአ) ከ30 ዓመት በኋላ ወደ ትውልድ አገሬ ኢትዮጵያ ስመለስ መስቀልን ከነክብሩ አገኘሁት።
ኑሯቸውን በአሜሪካ ቴክሳስ ያደረጉት ወይዘሮ የምስራች ዮሴፍ የ13 ዓመት ታዳጊ እያሉ ነበር ከኢትዮጵያ በመውጣት ባህር ማዶ የደረሱት።

ወይዘሮ የምስራች ከኢትዮጵያ ከወጡ በኋላ ላለፉት 30 ዓመታት ወደ ትውልድ አገራቸው ሳይመለሱ በአሜሪካን አገር ኖረዋል።

በአሜሪካ ቆይታቸው 4 ልጆችን ማፍራታቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ የምስራች፤ በዘንድሮው የመስቀል በዓለ መስቀል አደባባይ በመገኘት ከልጆቻቸው ጋር አክብረዋል።

"መስቀልን ከነ ክብሩ በአገሬ ምድር ኢትዮጵያ በመስቀል አደባባይ ባሸበረቀ መልኩ ከልጆቼ ጋር ተገኝቼ በማክበሬ ደስታዬ ወደር የለውም" ይላሉ።

ሌሎች በውጭ የሚኖሩ የዳያስፖራ አባለትም ከቤተሰቦቻቸው ጋር በእንዲህ አይነት በዓላትን ማክበር፣ ለልጆቻቸውን ስለ ኢትዮጵያ ባህልና ማንነት ማሳወቅ እንዳለባቸው ይናገራሉ።

"የትም የትም ኑር የመጨረሻ መዳረሻህ አገርህ ነች" የሚሉት ወይዘሮ የምስራች፤ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ሰላምና ህልውና በጋራ ሊቆሙ ሊገነቧትም ይገባል ነው ያሉት።

ልጆቻቸው ናኦሚ ዴካርቲ እና ጆሽዋ ዴካርቲም ከእናታቸው ጋር መስቀልን በኢትዮጵያ በማክበራቸው የተለየ ስሜት አንዳሰደረባቸው ይናገራሉ።

"በኢትዮጵያ መስቀል ድንቅ ነው፣ የተዋበና ያሸበረቀ በዓል ነው፤ በተመለከትነው ሁሉ የደምመናል" ብለዋል።

በተመሳሳይ እንደ ወይዘሮ የምስራች ቤተሰብ ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሌሎች ታዳጊዎችም በመስቀል በዓል አከባበር አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

"ኢትዮጵያ ውበት በአደባባይ የሚደምቅባት ድንቅ አገር" ሲሉም ታዳጊዎቹ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም