ኢትዮጵያውያን በዓላትን ስናከብር የአንድነት ቃላችንን በማደስ ሊሆን ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን በዓላትን ስናከብር የአንድነት ቃላችንን በማደስ ሊሆን ይገባል
ጭሮ/ ነቀምት/ ጅማ ፤ መስከረም 17/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን በዓላትን ስናከብር የአንድነት ቃላችንን በማደስና የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ሊሆን እንደሚገባ ተመለከተ።
የመስቀል በዓል በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
የደመራ በዓል በጭሮ ከተማ በተከበረበት ወቅት የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስና የቅዱስ ሶኖዶስ አባል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ እንጦንስ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሀገራችን በችግር ውስጥ ብትሆንም የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ ስርዓቱን ጠብቆ በድምቀት እየተከበረ ነው።
ቤተክርስቲያን ሁሌም የኢትዮጵያ ደህንነትና ሰላም እውን እንዲሆን ልመና ታቀርባለች ብለዋል፡፡
ምዕመኑም ለሀገርና ሰላም በመፀለይ፣ ራሱንና አካባቢውን በመጠበቅ ይህን ጊዜ እንዲያሳልፍ መልእክት አስተላፈዋል፡፡
የጭሮ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ማሩፍ ኢማም በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የአንድነት ቃላቸውን በማደስ በመተሳሰብና በፍቅር የሚኖሩባትን ሀገር በመጠበቅ እንዲያከብሩ አመልክተዋል፡፡
ሀገራችን አሁን ያለችበት ችግር የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጉዳይ በመሆኑ በዓሉን ስናከብር ለሀገር ሰላም መከበር መትጋትና የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት ከሀይማኖት አባቶችና ተከታዮች ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የጭሮ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ሚካኤል ዳኜ በበኩላቸው፤ በዓሉ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት መሰራቱን ገልጸዋል።
በዚህም የመስቀል ደመራው ስነ-ስርዓት ያለምንም የፀጥታ ችግር መከናወኑን አስታውቀዋል።
የበዓሉ ታዳሚ አቶ ዳንኤል ሞገስ በሰጡት አስተያየት፤ ህዝበ ክርስቲያኑ ይህን በዓል ሲናከብር ሀገራችን ከገጠማት ችግር ትላቀቅ ዘንድ ልመናና ፀሎት በማድረግ እንዲሁም የተቸገሩትንና የተፈናቀሉ ወገኖችን በመርዳት መሆን አለበት ብለዋል፡፡
ወጣት ዳንኤል ታደሰ በበኩሉ ፤ ከከተማዋ ወጣቶች ጋር ሌለውን የህብረተሰብ ክፍል በማስተባበረ የመስቀል ደመራ በዓል በሰላምና በድምቀት እንዲከናወን የድርሻቸውን መወጣታቸውን ገልጿል፡፡
በተመሳሳይ የመስቀል ደመራ በዓል በነቀምቴ በተከበረበት ወቅት የምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መላኬ ገነት ቆሞስ ወልደ ገብርኤል አበበ ፤ህዝበ ክርስቲያኑ እንኳን ለመስቀል ደመራ በዓል አደረሳችሁ ብለዋል።
መስቀል የሠላም፣ የፍቅር፣ የመዳን፣ የሕይወት፣ የዕርቅ እና የነፃነት ምልክት በመሆኑ መላው ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን አጠናክረው ይህንን የፈጣሪን ቃል ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ባህሩ ኤባ፤ ለእምነቱን ተከታዮች እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።
" የዘንድሮው የመስቀል በዓል ልዩ የሚያደርገው ሀገራችን በውስጥና ውጭ ጠላቶች ተወጥራ ባለችበት ይህን ሁሉ በመቋቋም በሠላም መከበሩ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
የእምነቱ ተከታዮች እና መላው የከተማው ነዋሪዎች አንድነታቸውን አጠናክረው ጥንት አባቶቻችን ነፃነቷን ጠብቀው ያቆዩልንን ሀገር ከመበታተን መጠበቅ አለብን ብለዋል።
የከተማው ገነት ኢየሱስ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ቄስ አሸብር ተስፋዬ፤ ሕዝቡ እግዚአብሔርን በማስታወስ ሁሉም እርስ በእርሱ ይቅር ባይነትን በማዳበር በሀገሪቱ ሠላም እንዲሰፍን የእምነት አስተምሮዎችን ማክበርና መጠበቅ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል አቶ ዴሬሳ በንቲ በሰጡት አስተያየት፤ በመካከላችን የመተሳሰብ፣ መቻቻል፣ መደጋገፍ እና መፈቃቀር ባህልን አጠናክረን ሀገሪቱን መጠበቅ ይኖርብናል ብለዋል።
የመስቀል ደመራ በዓል በተመሳሳይ በጅማ ከተማ በደማቅ ሃይማኖታዊ ስነስርዓት ተከብሯል።