የመስቀል በዓል በሱዳን በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነ-ሥርዓቶች በድምቀት ተከብረ - ኢዜአ አማርኛ
የመስቀል በዓል በሱዳን በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነ-ሥርዓቶች በድምቀት ተከብረ
መስከረም 17 /2014 (ኢዜአ) የመስቀል በዓል በሱዳን ካርቱም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ደብረ-ሠላም መድሃኒዓለም ቤተክርስቲያን የሃይማኖት አባቶችና የዕምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነ-ሥርዓቶች በድምቀት ተከብሯል፡፡
በስነ ሥርዓቱ ላይ በሱዳን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባለሙሉስልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ተገኝተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልእክታቸውም የመስቀል በዓል ለኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን በተ.መ.ድ የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት የተመዘገበ ለመላው የሠው ልጆች ሃብት ነው ብለዋል፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ የታሪክ እና የተፈጥሮ ሃብቶች ባለጸጋ እንደሆነች ገልጸው፤ ሆኖም ግን ህዝቧቿ ከድህነትና ከስደት ያልተላቀቀ መሆኑን ፣ አገራችን የተፈጥሮ ሃብቷን አልምታ ከድህነት እንዳትወጣ በተለያየ ጊዜ ከውስጥና ከውጭ የሚነሱ ጠላቶች ፈተና እንደሆኑባት አንስተዋል፣
በአሁኑ ወቅት ዘርን እንደ ጥፋት መቀስቀሻ የሚጠቀሙ ሃይሎች ጠባብ የቡድን ፍላጎታቸውን ለማሟላት ሕዝባችንን እርስ በእርስ ለማባላትና አገር ለማፍረስ እየሰሩ መሆኑን አስረደተዋል፡፡
ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያዊያን በዘርና በሃይማኖት ሳይለያዩ አንድ ሆነው ለአገራቸው ሠላምና አንድነት በጋራ መቆም እንደሚገባ መግለጻቸውን በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሴ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።