ቀጥታ፡

የሚመሰረተው መንግስት የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ይፈታልናል ብለን እንጠብቃለን--- የሲቲ ዞን ነዋሪዎች

መስከረም 16/2014-(ኢዜአ) የሚመሰረተው አዲስ መንግስት በአካባቢያቸው የሚያጋጥሙ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ይመልሳል ብለው እንደሚጠብቁ በሶማሌ ክልል የሲቲ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ እና የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ዑስማን ከሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን ነዋሪዎች ጋር በልማትና በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይ የሽንሌ ወረዳ አዛውንት አቶ መሐመድ አህመድ ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ዞኑ ለኢትዮጵያ ዕድገትና ልማት እንዲሁም ለወጪና ገቢ ንግድ እንቅስቃሴው አስተዋጽኦ እንዲኖረው እየተሰራ ነው ።

ይሁንና ዞኑና ህዝቡ የልማቱና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ ስላልሆነ አዲስ የሚመሰረተው መንግስት እነዚህ ጉዳዮች ላይ ሊያተኩር እንደሚገባ ተናግረዋል።

"ዞኑ ለልማት ካለው ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አንፃር የህዝቡን ጥያቄዎች ትርጉም ባለው መንገድ መመለስ ከአዲሱ መንግስት ይጠበቃል" ያሉት ደግሞ ሌላኛው አዛውንት ሐጂ ሙሴ መይጋን ናችው። 

"በአካባቢው በቂ መሠረተ ልማቶች የሉም፤ ዞኑ ከፍተኛ የከርሰ ምድር ውሃና ለም መሬት ቢኖሩትም የመስኖ ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም" ብለዋል። 

የጋራ መኖሪያ ቤቶችና መንገዶች ባለመገንባታቸው የዞኑ ሠራተኞች በአካባቢው ለመኖር አይፈልጉም፤ በዚህም ነዋሪዎች ለመልካም አስተዳደር ችግሮች እየተዳረጉ ይገኛል" ብለዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፈው የሽንሌ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ሃሰን ጣኢር እንደተናገረው የተማረው የአካባቢው ወጣት እየገጠመው ያለው የሥራ አጥነት ችግር እንዲፈታ ጠይቋል።

በተለይ የዞኑን ወጣት በፌዴራል ደረጃ የወጣቶች ፈንድ ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት መጠናከር እንዳለበት አስገንዝቧል።

የዚሁ ወረዳ ነዋሪ ወጣት አብዲ ኡስማን በበኩሉ ጥያቄዎችን ለመንግስት ከማቀረብ ጎን ለጎን በልማትና የዞኑን ሰላም በማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ ኃላፊነቱን ለመወጣት ዝግጁነቱን አረጋግጧል።

በተለይ ወደዞኑ ሰርገው በመግባት ሽብርና ሁከት ለመፍጠር የሚሞክሩ አካላትን ከፍትህና ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው እንደሚከላከሉ ወጣቱ ተናግሯል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኢብራሂም ኡስማን ለነዋሪዎች ጥያቄ በቅደም ተከተል መፍትሄ ለመስጠት የክልሉ መንግስት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

"ዞኑ ያለውን ሰው ሰራሽና እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ጥቅም ላይ በማዋል ለዜጎች ጥያቄ ትርጉም ያለው መልስ ይሰጣል" ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ዞኑን ከድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክና ሌሎች ሁለንተናዊ ልማቶች ጋር በማስተሳሰር እንደሚሰራ አመልክተዋል። 

የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አደም ፋራህ በበኩላቸው መንግስት መሰረተ ልማትን በፍትሃዊነት በማዳረስ የአርብቶ አደሩን ህይወት ለመለወጥና የእንስሳት ሃብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚሰራ ገልጸዋል። 

በአሁኑ ወቅትም መንግስት ለህግ የበላይነት፣ ለዘላቂ ሰላም እና ልማት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም