በአማራ ክልል ባለፉት አመታት የተከናወኑ የግብርና ልማት ስራዎች ምሁራንን ያሳተፉ እንዳልነበሩ ተገለፀ

75
ባህር ዳር ነሀሴ 10/2010 በአማራ ክልል ባለፉት አመታት የተከናወኑ የግብርና ልማትና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ  ስራ የዘርፉ ምሁራን ያሳተፈ ባለመሆኑ የተገኘው ውጤት የሚፈለገውን ያህል እንዳልሆነ ምሁራን ገለጹ። “እምቅ የተፈጥሮ ጸጋ ወደ ዘመናዊ ግብርና ልማት ለማሸጋገር የምሁራን ተሳትፎ  መተኪያ የለውም” በሚል መሪ ሃሳብ  የክልሉን  የዘርፉ ምሁራን ያካተተ የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው። ምሁራን በውይይቱ ላይ እንደገለፁት በክልሉ እስካሁን ሲከናወኑ የነበሩት የግብርና ልማትና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ አብዛኛዎቹ ስራዎች በፖለቲካ አመራር ብቻ ሲተገበሩ የቆዩ ናቸው። በመሆኑም የተከናወኑ የተፈጥሮ ሃብት ስራዎችም ሆኑ ሌሎች የሰብልና የፈራፍሬ ልማት ስራዎች ክልሉ ካለው የመልማት እምቅ አቅም አኳያ የተገኘው ውጤት አነስተኛ ሊሆን ችሏል። ምሁራኑ የተለያዩ ጥናቶችን ያቀረቡ ሲሆን ባቀረቡት ጥናት መሰረት እስካሁን የተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ስራው መከናወን ከነበረበት ከግማሽ በታች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችም የጥራትና የአቅርቦት ችግሮች እንደነበሩባቸው ምሁራኑ አረጋግጠዋል። በክልሉ በተከናወኑ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎች ዙሪያ ጥናት ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሃና መሬት ማዕከል ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር ጌቴ ዘለቀ እንደገለጹት የአማራ ክልል የተፈጥሮ ሃብት ጥብቃ ስራን ማከናወን ከጀመረ 43 ዓመታትን አስቆጥሯል። በ1966 ዓ.ም በክልሉ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የደረሰውን ችግር ለመቋቋም ሲባል የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ መጀመሩን ያወሱት ዶክተር ጌቴ እስካሁን የተከናወነው ስራ 43 በመቶ ብቻ መሆኑን ገልፀዋል። ''የክልሉን የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ መከናወን ካለበት ከግማሽ በላይ ያልተከናወነው  ስራው በባለሙያዎች ባለመመራቱ ነው'' ብለዋል። ''ሲከናወኑ የነበሩት የልማት ስራዎች ሙያዊ አሰራር ሳይሆን ፖለቲካዊ  አሰራር ብቻ በመሆናቸው በጥራትም ሆነ በሽፋን ደረጃ ወደ ኋላ ቀርቷል'' ነው ያሉት። “ችግሩን  በመሰረታዊነት ለመቅረፍ ምሁራንን ያሳተፈ ስራ አስፈላጊ ነው፤ ምሁራንን ያሳተፍ ውይይት መደረጉ ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል፤ በተግባርም አብረው እንዲሰሩ ማሳተፍ ያስፈልጋል” ነው ያሉት። የዘርፉ ምሁራን ያላቸውን አቅም ለህብረተሰባቸው ለማዋል ወደ ኋላ እንደማይሉም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል። ''ክልሉ ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ምቹና ሰፊ መሬት ቢኖረውም አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂን የመጠቀም ዝንባሌው አነስተኛ ስለሆነ ምርቱ ከእጅ ወደ አፍ ያልዘለለ ነው ያሉት'' ደግሞ በአትክልትና ፍራ ፍሬ ምርት ዙሪያ ጥናት ያቀረቡት የጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህር ፕሮፌሰር  ደርበው በላይ ናቸው። ክልሉ አትክልትና ፍራፍሬን በማልማት ረገድ ከራሱ አልፎ ለሌሎች መትረፍ ሲችል አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን አርሶ አደሩ ለራሱም በቂ የሆነ ምርት እንደማያገኝ ተናግረዋል። ለዚህም ሳይንሳዊ አሰራሩን ተከትሎና ለየመልከዓ ምድሩ ተስማሚ የሆነ ምርጥ ዘር መጠቀም አለመቻልና ከባህላዊ የአመራረት ዘዴ አለመላቀቅ ተጠቃሽ ምክንያት  እንደሆነ አብራርተዋል። ከዘርፉ ተገቢውን ምርት ለማግኘት ከተፈለገ ምሁራንን ያሳተፈ ስራ መስራት አማራጪ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ያስረዱት ዶክተር  ደርበው “ምሁራንም  ህብረተሰባቸውን ለማገልገል ዝግጁ ነን “ብለዋል። የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግስቴ በበኩላቸው እስካሁን የተሰራው የግብርና ልማት ስራ የምሁራንን አቅም  በተደራጀ መልክ  መጠቀም ያልተቻለበት እንደነበር ተናግረዋል። በተለይ በግብርና ባለሙያዎች ላይ የሚስተዋለው የክህሎትና የእውቀት ክፍተት እየሰፋ መምጣቱን ገልፀው ይህን ክፍተት ለመሙላት ቢሮው ምሁራንን ያሳተፈ ስራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የውይይት መድረኩ ዓላማም  ምሁራን የክልሉን  ነባራዊ ሀኔታ በጥናት አስደግፈው በማቅረብ  የሚያስቀምጡትን የመፍትሄ ሃሳብ ወደ ተግባር ለመቀየር  ነው። ለሁለት ቀናት በሚቆየው የውይይት መድረክ ላይ ከ50 በላይ የክልሉ ተወላጅ የዘርፉ ምሁራንና የክልሉ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም