የተቀበረ እውነት እና ኢትዮጵያ

454

በቀደሰ ተክሌ (ሚዛን አማን ኢዜአ)

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የደመራ በዓል በየዓመቱ በሃይማኖታዊ ስርአት በደመቀ ሁኔታ ይከበራል። ዛሬ ያከበርነው የደመራ በዓል የእውነት ፍለጋ በዓል ነው ማለት ይቻላል።

ብርሃንን ከጨለማ፣ እውነተኛን ከሐሰተኛ፣ ሀቅን ከተንኮለኛ ለመለየት የተደረገ ጥበብ። ነገርን ከስሩ እንዲሉ እስኪ ወደዚህ ጉዳይ ለመድረስ እንደርደር።

ኢየሱስ ክርስቶስ የምድር ቆይታውን የቋጨው በእንጨት መስቀል ላይ ነው።

ዘመኑም 33ኛ ዓ.ም ሲሆን እውነትን ባስተማረ፣ አበርክቶ ባበላ፣ ድውያንን ከህመማቸው በፈወሰ የቀኑት አይሁድ ምስጋናን ሳይሆን መከራን፤ ክብርን ሳይሆን ሞትን ፈረዱበት።

ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ቆይታው በርካታ ተዓምራትን አድርጓል። በእዚህ ተግባሩ ተንኮለኞቹ ያዩታል እንጂ አያምኑትም ነበር።

ግን እውነት እንደሆነ ልባቸው ያውቃል። ምክንያቱም በመስቀል ላይ ሰቅለውት ከሞተ በኋላ መቃብሩ በወታደሮች እንዲጠበቅ ነው ያደረጉት።

ይህን ሲያደርጉ እንደሚነሳ ቀድሞ ተናግሮ ነበርና እንዳይነሳ ለማድረግ ነው። እያወቁ አለማወቅ፤ እያመኑ አለማመን እንዲህ ነው። ልብ ሲደነድን እውነትን እንደ እውነታው ከመቀበል ይቆጠባል። 

የአይሁዳዊያን ተንኮል በዚህ ብቻ አያበቃም። ወታደሮቹ መቃብሩን እየጠበቁ ቢሆንም የመቃብሩን መክደኛ ማንም ሰው ሳይነካው ክርስቶስ ተነስቶም ሌቦች ሰረቁ እንበል ተባባሉ እንጂ እውነቱን ለመግለጥ አላሰቡም።

እውነትን በልባቸው ውስጥ ቀብረው ለማስቀረት ቢሞክሩም የመነሳቱ ዜና ተገልጦ ለዓለም ተዳርሷል።

በትንሣኤው የተበሳጩ በተዓምራቱ ተናደዱ ባይቀበሉትም እንኳ አሁንም ያምኑታል።

የማመናቸውና ማወቃቸው ሌላኛው ማሳያ የነካው ሁሉ እንደሚፈውስና ተዓምር እንደሚያደርግ መረዳታቸው ነው። ከዚህም አንዱ የተሰቀለበት መስቀል ነው።

የወንበዴ መቅጫ የነበረው መስቀል ኢየሱስ ስለ ተሰቀለበት ታሪኩ ይቀየራል ብለው አመኑ፣ በርሱ ያመኑት በመስቀሉ ሊፈወሱ ተዓምራትም በመስቀሉ ሊደረግና ሊመኩበት ይችላሉ በሚል እምነት ተነሳስተውም ተንኮል አሰቡ።

መስቀሉን ለመሸሸግና ጭራሹን እንዲጠፋ ለማድረግ ተስማሙ። እውነትን ስለ እውነትነቱ ቀበሩት፤ የኛ ካልሆነ በሚል እውነትን በሀሰት ተኩ።

መስቀሉን ቆፍረው ከቀበሩት በኋላ የከተማ ቆሻሻ በሙሉ እዛው እንዲጣል ተወሰነ። በእዚህም መስቀሉ ለዘመናት ተሰውሮ ቆየ።

ዓለም እውነት ቀባሪ ብቻ ሳይሆን እውነት ፈላጊዎችም የሚኖርባት ናትና መስቀሉን አጥብቃ የምትሻ ንግስት ተገኘች፤ “ንግስት እሌኒ”።

ንግስት እሌኒ በብዙ ፍለጋ ላይ ብትሆንም መስቀሉን ቶሎ ልታገኝ አልቻለችም። “እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል” እንዲሉ ከፍለጋ ብዛት ልታገኝ የምትችልበትን አቅጣጫ የሚጠቁም አረጋዊ ኪሪያኮስ ተገኘ።

ከሦስቱ ተራሮች በአንደኛው ነው መስቀሉ ያለው በማለት ጠቆመ፤ የተዳፈነ እውነት። 

አሁን ንግስት እሌኒ በጥበብና በእምነት መስቀሉን ለማግኘት ደመራ አስደመረች፤ እሳት ተለኩሶ እጣን ተጨመረበት።

በዚህን ጊዜ የእጣኑ ጢስ ወደ ላይ ከፍ ይልና ተመልሶ ከሦስቱ ተራሮች አንደኛው ተራራ ላይ አረፈ /መስቀሉ ያለበትን አመለከተ።

ለዘመናት ተቀብሮ የቆየው መስቀል ተቆፍሮ እየበራ ወጣ፤ ብርሃኑም ለዓለም ሁሉ አበራ። 

ይህን አስባ ዛሬ ድረስ የደመራና የመስቀል በዓልን የምታከብረው ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ ተመሳሳይነት አለው ማለት ይቻላል።

መስቀሉ በቆሻሻ ተራራ እንደተዳፈነው ሁሉ የኢትዮጵያም እውነት ተቀብሯል፤ የተንኮለኞች የሐሰት ሴራ ተከምሮበት ከብዙ የዓለም ህዝቦች እይታ ርቋል።

ስለማያውቁ ሳይሆን የአይሁድ አይነት ምቀኝነት በውስጣቸው ስላለ ነው እውነትን ቀብረው ለሐሰትና ለሀሰተኞች እያጎበደዱ ያሉት።

እንደ እሌኒ ያሉቱ አያሌ ልጆቿ ደግሞ እውነትን ለማውጣት ቁፋሮ ላይ ናቸው።

እወነቱ ተገልጦ የጠላት ተንኮል ሲፈርስ የኢትዮጵያ ብርሃን ለአፍሪካ ይበራል፤ በዓለም ድንቅ ሆኖም ይታያል። የተቀበረው የኢትዮጵያ እውነት ሲገለጥ ማዕቀቡም ግድቡም ከተንኮለኞች አይን ይርቃል።

እርግጥ ነው ኢትዮጵያ ጥበብን፣ ታሪክን፣ መልካምነትን፣ ፍቅርና ደግነትን የሰጠች ቸር አገር ብትሆንም ለክርስቶስ እንደሆነው ሁሉ በክፉ ተቀይሮባት የመፍረስና መጥፋት ቅጣት ተፈርዶባታል።

ኢትዮጵያ እውነት ናትና አትፈርስም እውነቷም ሊዘገይ ይችል ይሆናል እንጂ በተንኮለኞች ሴራ ተቀብሮ አይቀበርም።

አይሁድ ስለ ክብራቸውና ከእኛ ውጭ ማን በሚል ትዕቢታቸው ኢየሱስን ሰቅለው ገድለው የተሰቀለበትን ቀብረው እንደ ደበቁት ሁሉ እኛ ብቻ ካልመራን ባዮች ኢትዮጵያን ዘርፈው በልተው ከጨረሷት በኋላ እውነቷን ቀብረዋል።

መስቀሉን የቀበሩት ጠፍተዋል፤ መስቀሉ ግን እውነት ነውና ዛሬም አለ። ከመስቀሉ ግማዶች መካከል የአንዱ ባለቤት እውነቷ፣ ሀቋ የተቀበረባት ኢትዮጵያ ነች።

ቀባሪ ጠላቶቿ ጊዜያቸው ደርሶ ከምድር ይጠፋሉ ኢትዮጵያ ግን ለዘለዓለም ትኖራለች።

አይሁድ የቀበሩት መስቀል በአንድ ጊዜ አልተገኘም ለብዙ ዘመናት ቆይቶ በብዙ ፍለጋ ነው ተገኝቶ የወጣው ።

የኢትዮጵያ ሰላምም በአንድ ጀምበር እንዲገኝ መፈለግ የዋህነት ይሆናል።

ለዚህ አመክንዮ ደግሞ ብዙ ቆሻሻ ተከምሮበታልና ነው።

የዘረኝነት ቆሻሻ፣ ሙስናና ሌብነት፣ የተንኮልና ምቀኝነት፣ ያለመከባበርና እኔ ብቻ ልጠቀም የቆሻሻ ክምር።