ህብረተሰቡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከል አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተጠየቀ

143

አዲስ አበባ፣  መስከረም 16/2014 ( ኢዜአ) ህብረተሰቡ የመስቀል በዓልን በሚያከብርበት ወቅት ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከሚያጋልጡት ተግባራት ራሱንና ሌሎችን እንዲከላከል ጥሪ ቀረበ።

ህብረተሰቡ የመስቀል በዓልን በሚያከብርበት ወቅት ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከሚያጋልጡ ተግባራት ራሱንና ሌሎችን ለመከላከል አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል።

አፍሪ ኢቭንትስ ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ እና ከ ዩ.ኤስ.ኤይድ ጋር በመተባበር በአዘጋጀው የአደባባይ ላይ የግንዛቤ መስጫ መርሃ ግብር፤ የመስቀል በዓልን ምክያት በማድረግ በዓሉን ለማክበር በሚደረግ የሰዎች መሰባሰብ ምክንያት ሊፈጠር የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጠይቋል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እየተስፋፋና የሟቾችም ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን መረጃዎች እንደሚያሳዩ አመልክቷል።

አፍሪ ኢቭንትስ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በአሁን ወቅት ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ከማድረግ እየተዘናጋ መጥቷል። በተለይም ማህበረሰቡ በተሳሳተ ግንዛቤዎች ክትባቱን ሳይወስድ እንደሚቀር ይስተዋላል።

በቅርብ እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚጠቁሙትም በአገሪቷ በአሁኑ ወቅት በበሸታው እየሞቱ ካሉ ሰዎች ውስጥ አብዛኞቹ ያልተከተቡ መሆናቸውን አመልክቷል።

ስለሆነም ህብረተሰቡ ስለ ኮሮና ቫይረስ ክትባት ጠቀሜታ ትክክለኛውን ግንዛቤና መረጃ አግኝቶ በመከተብ ራሱንም ሆነ ቤተሰቡን ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠብቅም ጠይቋል።

ሦስቱ ተቋማት በመተባበር የሚያካሂዱት ቅስቀሳ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ተሽከርካሪዎች በመዘዋወር በልዩ ልዩ ትርኢቶች በመታጀብ ነው።  

በዚህ ወቅት ህብረተሰቡ የሚተላለፉትን የጤና መልዕክቶች በመገንዘብና ተግባራዊ በማድረግ በዓሉን በሚያከብሩበት ወቅት ራሱንና እና ሌሎችን እንዲጠብቅ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

በተለይም የክትባቱን ጠቀሜታ ተረድቶ ወደ መከተቢያ ጣቢያ እንዲያመራ የሚያበረታታ መሆኑም ተመልክቷል።

በዚህም ህብረተሰቡ በየትኛውም ቦታ ላይ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ወረርሽኙን እንዲከላከልና ክትባቱን በመውሰድ ራሱንና ሌሎችንም እንዲጠብቅ ጥሪ ቀርቧል።