በደቡብ ክልል በዘመናዊ አሰራር የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው

174

ሃዋሳ፣ መስከረም16/2014  (ኢዜአ)  በደቡብ ክልል በተመረጡ ሰብሎች ምርታማነትን ለማሳደግ በ4 ሺህ 200 ኩታ ገጠም መሬት ለተደራጁ አርሶ አደሮች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ አስታወቀ።

በሀላባ ዞን አቶቴ ኡሎ ወረዳ በ2013/014 የመኸር ወቅት የተከናወነ የበቆሎ ኩታ ገጠም እርሻ ልማት ተጎብኝቷል።

በመስክ ምልክታ መርሃ-ግብሩ ላይ በኤጀንሲው የደቡብ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ፈጠነ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት ኤጀንሲው ለአርሶ አደሩ ማነቆ የሆኑትን ችግሮች በመለየት ለመፍትሄው ፕሮጀክት ቀርፆ እየሰራ ነው።

"የአርሶ አደሩ አንዱ ችግር ለገበያና ለአሰራር በማያመች ሁኔታ በተበጣጠሰ ማሣ ላይ እርሻውን ማከናወን ነው” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ችግሩን ለመፍታት ኩታ ገጠም አሰራርን በመጠቀም ለገበያ የሚፈለጉትን በጋራ ማልማት እንዲችል የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑን አስረድተዋል።

"ከድጋፎቹ 6 ሺህ ለሚጠጉ የግብርና ባለሙያዎች እና ለ345 ሺህ የክልሉ አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴና ጠቀሜታው ላይ ስልጠና በመስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ አንዱ ነው" ብለዋል።

በክልሉ 66 ወረዳዎች የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው ተለይተው በተደራጁ 4ሺህ 200 ኩታ ገጠም ማሳዎች ላይ አርሶ አደሮች የሰሊጥ፣ ጤፍ፣ ስንዴ እና በቆሎ ሰብሎችን እንዲያለሙ መደረጉን ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ የግብርና ግብዓት በቅርበት እንዲያገኝ የመሸጫ ማዕከላትን በአካባቢው በመገንባትና የገበያ ትስስር በመፍጠር ድጋፍ መደረጉን አስረድተው በዚህም ምርታማነትን በሄክታር በአማካይ ከ15 እስከ 20 በመቶ ማሳደግ መቻሉን አስታውቀዋል።

በ2013/2014 ምርት ዘመን 182 ሺህ ሄክታር መሬት በአራቱ ሰብሎች በኩታ ገጠም መልማቱንና የተሻለ ምርት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

በመስክ ጉብኝቱ ላይ የተገኙት የሀላባ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር መሐመድ ኑርዬ በበኩላቸው "የኩታገጠም ልማትን በማስፋፋት ምርታማነትን ለማሳደግና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

ለልማቱ ስኬታማነት ሜካናይዜሽንን ከማበረታታት ባለፈ የተጀመሩ ምርጥ ተሞክሮዎችን በዞኑ ሁሉም አካባቢዎች የማስፋፋት ሥራ እንደሚሰራም አመልክተዋል። 

የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሀጂ ኑርዬ ኤጀንሲው በቅርበት በሚያደርገው ድጋፍ የኩታገጠም ግብርና ልማት ስራዎች አበረታች እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

"ይሁንና በዘንድሮ የመኸር እርሻ 75 በመቶ የሚሆነውን ማሣ በኩታ ገጠም ለማልማት ታቅዶ ባጋጠመ የዝናብ እጥረት ምክንያት 25 በመቶውን ብቻ ለማሳካት ተችሏል" ብለዋል።

ኃላፊው እንዳሉት በዞኑ በ2013/2014 የመኸር እርሻ እንቅስቃሴ ከለማው 27 ሺህ 400 ሄክታር መሬት ላይ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

በሃላባ ዞን አቶቴ ኡሉ ወረዳ ዬዬ ቀበሌ አርሶ አደር ጀማል ሀጂ መሀመድ በሰጡት አስተያየት ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ 32 አርሶ አደሮች በ54 ሄክታር መሬት ላይ በቆሎን በኩታ ገጠም አልምተው ምርት ለመሰብሰብ መቃረባቸውን ተናግረዋል።

የሰብሉ ቁመና በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝና ካለፉት ሁለት ዓመታት የተሻለ ምርት እናገኛለን ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

በኩታ ገጠም እርሻ የተሳተፉት ሌላው አርሶ አደር ሸምሱ ከድር በበኩላቸው ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በቆሎ በጋራ በማልማታቸው ብዙ ለውጥ ማየታቸውን ነው የገለጹት።

ከልማቱ በሄክታር 60 ኩንታል ምርት እናገኛለን ብለው እንደሚጠብቁ ጠቁመው፣ በቀጣይም ምርትን ከሁለት እጥፍ በላይ ለማሳደግ የያዙት ውጥን እንዲሳካ የእርሻ ትራክተር ማግኘት እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም