በአውስትራያ “የኢትዮጵያን እናድን” አባላትና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሃላፊዎች በውጭ ምንዛሬ ዙሪያ ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
በአውስትራያ “የኢትዮጵያን እናድን” አባላትና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሃላፊዎች በውጭ ምንዛሬ ዙሪያ ተወያዩ
መስከረም 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአውስትራሊያ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ "ኢትዮጵያን እናድን" ፋይናንስ አባላት በውጭ ምንዛሬ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ።
ውይይቱን የከፈቱት በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶ/ር ሙክታር ከድር "ኢትዮጵያ የልጆቿን ድጋፍ ከምንም በላይ በምትፈልግበት ወቅት ወደ ወደ ተግባር በመግባታቸው የ"ኢትዮጵያን እናድን" አባላትን አመስግነዋል።
አክለውም "ኢትዮጵያን እናድን" ወቅቱን የጠበቀና ትክክለኛ መድረክ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዳያስፖራ ተሳትፎና ቢዝነስ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ለማ ዋቀዮ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ምንዛሬ ምንጮች ውስን መሆናቸውን ጠቁመው፤ በዋነኛነት የውጭ ብድር፣ እርዳታ፣ የውጭ አቅርቦትና ሃዋላ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ከእነዚህም ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት የውጭ ብድርና እርዳታ መሆናቸውንና የውጭ አቅርቦት ገቢ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት የሚጠይቀውን ያህል አለመሆኑን መግለጻቸውን ከኤስ ቢኤስ አማርኛ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ሃላፊው አክለውም "የኢትዮጵያን እናድን ተነሳሽነት ትክክለኛም ወቅታዊም ነው ብለዋል።
የውጭ ምንዛሬ ክፍተቱን ለማሻሻልም ያስችላል፣ ካላችሁበት አገር ሆናችሁ ያላችሁን ገንዘብ ኢትዮጵያ ማስቀመጥ ትችላላችሁ፣ ይህን ማድረግ አገርን ማገዝ ነው፤የጥቁር ገበያው ከምጣኔ ሃብት ጉዳት አልፎ የሰው ሕይወትን ጭምር እያጠፋ ነው" ብለዋል።
"የኢትዮጵያን እናድን” አባላት ዶ/ር ከፋለ መኮንንና አቶ ግርማ ፈይሳ የኢትዮጵያን እናድን ተነሳሽነት ዓላማ፣ እስካሁን የተደረጉ እንቅስቃሴዎች፣ ታሪካዊና ወቅታዊ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና እርዳታን አስመልክተው ለታዳሚዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።