አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ጫና የሚቃወም ሠልፍ ከነገ በስቲያ በዋሽንግተን ይካሄዳል

87

መስከረም 15/2014(ኢዜአ) አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ጫና የሚቃወም  ሠላማዊ ሠልፍ በመጪው ሰኞ በዋሽንግተን ዲሲ ይካሄዳል።

በሠልፉ ላይ በአሜሪካና በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ይሳተፋሉ ተብሏል።

ሠልፉ የአሜሪካን ጫና ለመቃወምና እጇን ከኢትዮጵያ ላይ እንድታነሳ ለመጠየቅ መዘጋጀቱን የሠላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ግብረ ሃይል የዲሲ አስተባባሪ አቶ ጣሰው መላከህይወት ለኢዜአ ገልጸዋል።

ሠልፉ በዋይት ሀውስ፣ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትና የአሜሪካው ኬብል ኒውስ ኔትወርክ /ሲ.ኤን.ኤን/ የዋሽንግተን ዲሲ ቢሮ ፊት ለፊት ይካሄዳል።

በሠልፉ ላይ የአሜሪካን ያልተገባ ጫናና ጣልቃ ገብነት የሚቃወሙ መልዕክቶችም ይተላለፋሉ።

"አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የምታደርገውን ትክክል ያልሆነ ጣልቃ ገብነት እንቃወማለን፣ የመንግስትን እጅ በመጠምዘዝ ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ድርድር ይደረግ የሚለውን ሃሳብ አንቀበልም፣ ከሽብርተኛ ጋር አንደራደርም እና ጆ ባይደን ማዕቀብ ለመጣል የፈረሙት ውሳኔ የተሳሳተ ነው፤ ትዕዛዙን ይሰርዙ" የሚሉት በሠልፉ ከሚተላለፉ መልዕክቶች መካከል ይገኙበታል።

"አሜሪካ ከኢትዮጵያ ላይ እጅሽን አንሺ፣ አሜሪካ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ታክብር፣ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች፣ ሲ.ኤን.ኤን በኢትዮጵያ ጉዳይ የተሳሳተ ዘገባ እያሰራጨ ነው፣ ሲ.ኤን.ኤን የአሜሪካን ሕዝብ አታሳስት፤ ተአማኒና እውነተኛ ዘገባ አስተላልፍ" የሚሉ መፈክሮችም ተዘጋጅተዋል።

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ጫና እንድታቆምና እጇን እንድታነሳ የሚያሳስቡ ደብዳቤዎች ለዋይት ሀውስ፣ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ለሲ.ኤን.ኤን እንደሚሰጥም ነው አቶ ጣሰው የገለጹት።

በዋሽንግተን ዲሲ፣ ሜሪላንድ፣ ቨርጂኒያ፣ ፔንሲልቫኒያ፣ ማሳቹሴትስ፣ ኖርዝ ካሮላይና፣ ጆርጂያ፣ ኒውዮርክና በሌሎች የአሜሪካ ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሠልፉ እንደሚሳተፉም ጠቁመዋል።

"ቶርንቶን ጨምሮ በካናዳ የተለያዩ ግዛቶችና ከተሞች የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች በሠልፉ ይሳተፋሉ፤ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎችም ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል" ብለዋል አቶ ጣሰው።

ከሠልፈኞቹ በተጨማሪ ጥሪ የተደረገላቸው የአሜሪካ ኮንግረስና ሴኔት አባላት ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የገለጹት።

ሠላማዊ ሠልፉ ከነገ በስቲያ በኢትትዮጵያ ሠዓት አቆጣጠር ከቀኑ 10፡00 ሠዓት ጀምሮ ይካሄዳል።

አቶ ጣሰው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ማዕቀብ ለመጣል ያስተላለፉት ውሳኔ በአሜሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ቁጣ መቀስቀሱን ገልጸዋል።

"አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋን ዳግም ማጤን አለባት፤ የአሜሪካ ውሳኔዎች ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ ወዳጅነት የሚጎዳ እንደሆነም መረዳት ይገባታል" ብለዋል።

ዳያስፖራው በየሚኖርበት ግዛትና ከተማ ለሚገኙ የኮንግረስና ሴኔት አባላት የባይደን ውሳኔ የሕግ አውጪ ምክር ቤት አባላት ላይ ተጽዕኖ በሚፈጥሩ ግለሰቦች /ሎቢስቶች/ የተሳሳተ መረጃ ላይ የተመሰረተ መሆኑን እያስረዳ እንደሆነም ገልጸዋል።

"አሸባሪው ህወሓት ከኢትዮጵያ በዘረፈው ገንዘብ ሎቢስቶችን በመቅጠርና የተሳሳተ መረጃ በመስጠት በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና እንዲደረግ እያረገ ነው፤ ለሎቢስቶች የግፍ ገንዘብ እየሰጠ ነው" በሚል የሕግ አውጪ ምክር ቤት አባላቱ እንዲያውቁት እየተደረገ ነው ብለዋል።

አባላቱ ሁኔታውን በመረዳት ቀና ምላሽ እየሰጡ ነው ያሉት አቶ ጣሰው፤ በአሜሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ በሕግ አውጪ ምክር ቤት አባላት ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ግለሰቦች /ሎቢስቶች/ በመቅጠር የአገሩ ጥቅም እንዲከበር ግፊት እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለውን የተሳሳተ ፖሊሲ እንድታስተካክል የሚያደርጉት ጫና ተጠናክሮ እንደሚቀጠልም አክለዋል።

ከነገ በስቲያ በዋሽንግተን ዲሲ የሚካሄደው ሠላማዊ ሠልፍ የሠላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ግብረ ሃይል ዲሲ፣ የሲቪክ ተቋማት፣ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በጋራ ያዘጋጁት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም