የጥናትና ምርምር ሥራዎች ችግር ፈቺ፣ ለውጥ የሚያመጡና ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓት ሊሆኑ ይገባል

897

መስከረም 15/2014 (ኢዜአ) የጥናትና ምርምር ሥራዎች የማኅበረሰቡን ችግሮች በመፍታት ለውጥ የሚያመጡና ለፖሊሲ አውጪዎችም ግብዓት ሊሆኑ እንደሚገባ ተጠቆመ።

የስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት “ምርምር ለተቋማት ትስስር እና ለአገር ግንባታ” በሚል መሪ ሐሳብ የፓናል ውይይት አካሂዷል፡፡

ኢንስቲትዩት በውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ፣ በሠላምና ደህንነት እንዲሁም ውቅረ-መንግሥትና አገር ግንባታ ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ 

የተለያዩ አገራዊ፣ ቀጣናዊ እና ዓለምአቀፋዊ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ጥናቶችን እያካሄደ መሆኑን የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ቧያሌው ገልጸዋል።

ለመንግሥት ተቋማት የፖሊሲ ቀረጻና ምክረ-ሐሳቦች ከመስጠት አንስቶ ችግር ፈቺ ጥናቶችን በማካሄድ ጉልህ ፋይዳ ያላቸው ተግባራት በማከናወን ላይ እንደሚገኝም አክለዋል፡፡ 

ጥናትና ምርምሮቹ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፓለቲካዊ መስኮች ለውጥ እንዲመጣ ከማድረግ አኳያ የጎላ ሚና እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህልውና ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲረጋገጥ እውቀትን መሰረት ያደረጉ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ተሰርተው ሊተገበሩ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡

የአገር አንድነት እንዲጸና ለማድረግም ጥናትና ምርምሮች አስፈላጊ ናቸው ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።

በፓናሉ የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ ዶክተር ተስፋዬ በዛብህ፤ በአገሪቷ የተለያዩ ተቋማት በተለያየ ጊዜ የተሰሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ሊተገበሩ ይገባል ብለዋል፡፡

የሚሰሩ ጥናትና ምርምሮችም ሕዝቡ ውስጥ ገብተው መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ መሆን እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡

 ሌላው ጥናት አቅራቢ አቶ ወንድወሰን ንጉሴ፤ ተመራማሪዎች ለፖሊሲ ግብዓትና ለምክረ-ሐሳብ ሥራዎች ጠቀሜታ ያላቸውን ጠንካራ የምርምር ሥራዎች ማቅረብ እንደሚገባቸው አመልክተዋል፡፡

መንግሥትም ሆነ ውሳኔ ሰጪ አካላትም ለተመራማሪዎች ሐሳብ ጊዜና ቦታ ሰጥተው ተግባራዊ ሊያደርጉት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ ወንድወሰን ገለጻ አገሪቷ አሁን ካለችበት ሁኔታ እንድትወጣና ህልውናዋ እንዲከበር በዚህ ጉዳይ የሚሰሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ፋይዳቸው የጎላ ነው፡፡

ለዚህም ተመራማሪዎች ለአገር ህልውና መከበርና ሉዓላዊነት መጠበቅ ሊያግዙ የሚችሉ የጥናት ሥራዎችን ማከናወን ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡ 

በፓናል ውይይቱ ከበርካታ ተቋማት የተውጣጡ ምሑራንና ታዋቂ ሰዎች ተሳትፈዋል፡፡