የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እንደሚሰራ የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ገለጸ

67
ጋምቤላ ነሀሴ 9/2010 ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት እንደሚሰራ የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ገለጸ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት 11ኛ መደበኛ ጉባኤ ተካሂዷል፡፡ የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ቺቢ ቺቢ ለምክር ቤቱ ጉባኤ ባቀረቡት የ2010 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት  እንዳመለከቱት በከተማዋ በገቢ አሰባሰብ ፣በወጣቶች ሥራ እድል ፈጠራና በአረንጓዴ ልማት ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ በተለይም በከተማዋ 2 ሺህ 824 አንቀሳቃሾች ያሏቸው 617 ኢንተርፕራይዞችን በማደራጀት በማኒፋክቸሪንግ፣በግንባታ፣ በከተማ ግብርናና በንግድ ዘርፍ በማሰማራት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ ከተለያዩ የገቢ ምንጮች  40 ሚሊዮን 766 ሺህ ብር በመሰብሰብ ከእቅዶ ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ ክንውን መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡ በከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ዘርፍም 4 ሺህ 244 ቤተሰቦችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ክንውኑ ከ88 በመቶ  መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ሪፖርቱን ያደመጡት የምክር ቤቱ አባላት በበጀት ዓመቱ ክፍተት ናቸው ያሏቸውን አንሰተዋል፡፡ ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ወይዘሮ ባንቻየሁ ድንገታ እንዳሉት በከተማዋ የሚሰባሰበው ገቢ ለታለመለት አላማ ባለመዋሉ ከተማ አስተዳደሩ ደመወዝ  ለመክፈል የሚቸገርበት ሁኔታ ታይቷል፡፡ በከተማዋ በህገ ወጥ መንገድ የሚገነቡ ግንባታዎችንና ህገ ወጥ ንግድን በመከላከል በኩል የሚታየውን ክፍተት ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ የከተማዋን እድገት ለማስቀጠል ሁሉም በጋራ መስራት እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል፡፡ በከተማዋ በታራሚዎች አያያዝ፣ በንጹህ መጠጥ ፣በመሰረታዊ የሽቀጦች አቅርቦትና በሌሎችም ዘርፎች ችግሮች እንዳሉ የተናገሩት ደግሞ ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ኩዊች ዊው ናቸው፡፡ ከተማ አስተዳደሩ ህዝቡ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት በኩል በቀጣዩ በትኩረት መሰራት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ኡጆም ኡጁሉ በበኩላቸው "በከተማዋ የሚታየው የነጋዴዎች የግብር ቅሬታ፣ በቄራዎች በኩል የሚስተዋለው ባለተፈቀደ መልኩ የሚደረገው እርድ በህብረተሰቡ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ታሳቢ በማድረግ ችግሩ ሊፈታ ይገባል " ብለዋል፡፡ የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ ከምክር ቤቱ የተመለከተውን ክፍተት በቀጣይ በማስተካከል የህብረተሰቡን የልማት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በተገቢው ለመመለስ በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡ በጋምቤላ ከተማ ለሁለት ቀናት  ሲያካሄድ የቆየው የምክር ቤት ጉባኤ  የተለያዩ ሹመቶችንና ለተያዘው በጀት ዓመት እቅድ ማስፈጸሚያ ከ141 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በማጽደቅ ትናንት ተጠናቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም