ሕዝብ የጣለብንን አደራ እንተገብራለን

63

አዳማ፤መስከረም 15/2014(ኢዜአ) ምስረታውን ዛሬ ያካሄደው የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት አባላት በሕዝብ የተሰጣቸውን ሃላፊነትና አደራ በአግባቡ እንደሚወጡ ገለጹ።

ዛሬ በተካሄደው 6ኛው ዙር የጨፌ ኦሮሚያ የመጀመሪያው ጉባኤ፤ አዲሶቹ የምክር ቤት አባላትም በክልሉ ሕዝብ የተጣለባቸውን ሃላፊነት በቁርጠኝነት እንደሚወጡ ገልጸው፤ ሕዝቡ በብዙ ፈተና ውስጥ ሆኖ የሚመሰረተው መንግስት ከችግር እንደሚያወጣው ተስፋ በማድረግ ድምጽ እንደሰጣቸው ተናግረዋል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ካደረጉት የምክር ቤቱ አዲስ አባላት መካከል አቶ መሀመድ ዑመር ዑስማን የጭሮ ከተማ ተመራጭ ናቸው።

እንደ እርሳቸው ገለፃ የጭሮ ሕዝብ የመልካም አስተዳደር፣ የማሕበራዊና የኢኮኖሚ ችግሮች አሉበት።

"የመረጠኝ ሕዝብ እነዚህን ችግሮች ያቀልልኛል ብሎ በመሆኑ የጣለብኝን አደራ ለመወጣት ዝግጁ ነኝ" ብለዋል።

ሕዝቡ የሰጣቸውን አደራና ተስፋ ሙሉ በሙሉ እንዲፈጸም ያለማንም ቀስቃሽ ለመፈጸም መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ "ታሪካዊ የሚያስብል ብዙ መልክ አለው" ያሉት ደግሞ የጉጂ ዞን ተመራጭ ወይዘሮ ወርቄ ሮቤ፤በእነደዚህ አይነት የምርጫ ወቅት ሕዝብን መወከል መታደልም ትልቅ ፈተናም መሆኑን ነው የገለጹት።

ይሁንና ብዙ መስዋዕትነት ከፍሎ ድምጽ ለሰጠው ሕዝብ አይንና ጆሮ ሆነው ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

"ሕዝብ ትልቅ አደራና ሀላፊነት ሰጥቶን ነው እዚህ የመጣነው" ያሉት ደግሞ የምስራቅ ሀረርጌ ደደር ወረዳ ተመራጭ ወይዘሮ ሳሚያ አብደላ ናቸው።

ሕዝቡ ከችግር እንዳይወጣ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ቀድሞ የነበረው የጥቅም ትስስር አለመቋረጡ ነው ያሉት ወይዘሮ ሳሚያ፤ እንደ አንድ የጨፌ አባል እነዚህን የጥቅም ትስስሮች በማስወገድ ሕዝቡን በሀቀኝነት ለማገልገል መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።

የአርሲ ዞን መረቲ ወረዳ ተመራጩ አቶ አረባ ሁኔን ገመዳ ደግሞ "ሕዝብና አገርን ከማገልገል በላይ ትልቅ ክብር የለም፤ በመሆኑም የመንግስት እቅዶችን በመፈጸም ትልቅ ስራ ለመስራት ተዘጋጅተናል ነው ያሉት።

ጨፌው የአፈ-ጉባኤዎች ፣ የክልል ፕሬዚዳንትና ሌሎች ሹመቶችን አጽድቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም