በኢሉአባቦር ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ለሚገኙ አካል ጉዳተኞች ድጋፍ ተደረገ

78

መቱ፣ መስከረም 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢሉአባቦር ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ለሚገኙ አካል ጉዳተኞች አጋፔ ሞቢሊቲ ኢትዮጵያ በተባለ ግብረሰናይ ድርጅት ድጋፍ መደረጉ ተገለፀ፡፡

የዞኑ የአካል ጉዳተኞች ማሕበር ምክትል ሰብሳቢ አቶ አወቀ ዱባለ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

አካል ጉዳተኝነትን እንደፈጣሪ ቁጣና እርግማን የማየትና በቤት ውስጥ ደብቆ የማስቀመጥ ባህል ዛሬም ድረስ እንደሚስተዋል የተናገሩት አቶ አወቀ፤ “አካል ጉዳተኝነት በራሱ የችሎታ ችግር እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል” ብለዋል።

የተለያዩ የአካል ጉዳት ያለባቸው ወገኖች ለማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት እንዳይዳረጉ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የተለያዩ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ሕፃናትንና በተለያዩ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱ የተለያዩ የአካል ድጋፎች ላይ የሚሰራው የአጋፔ ሞቢሊቲ ኢትዮጵያ አስተባባሪ ሲስተር ሳባ ተክለማርቆስ በበኩላቸው አካል ጉዳተኞች ማንኛውንም ተግባራት ማከናወን እንደሚችሉ አስገንዝበዋል።

ድርጅቱ በአንደኛው ዙር ከ35 በላይ ለሚሆኑ የአካል ጉዳተኞች ከ460 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸውን የዊልቸርና የክራንች ድጋፍ ማድረጉንም ገልጸዋል።

የድጋፉ ተጠቃሚዎች ቤተሰቦች የነበረባቸው ጫና እንደሚቃለልላቸው ተናግረዋል።

በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች ከአምስት ሺህ በላይ የአካል ድጋፎች የሚያስፈልጋቸው ሰዎች እንደሚገኙ ከዞኑ ማሕበራዊ ዋስትና ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም