የበጋው የዝናብ ስርጭት መደበኛና ከመደበኛ በታች እንደሚሆን የብሔራዊ ሜትዮሮሎጂ ኤጄንሲ ገለጸ

151

አዳማ  መስከረም 14/2014 (ኢዜአ) በመጪው በጋ ሊኖር የሚችለው የዝናብ ስርጭት መደበኛና ከመደበኛ በታች መሆኑን የብሔራዊ ሜትዮሮሎጂ ኤጄንሲ ገለፀ።

ኤጄንሲው በመጪው በጋ ሊኖር የሚችለውን የአየር ጠባይ አዝማሚያ ትንበያ ይፋ አድርጓል።

ያለፈው የክረምት ወቅት የአየር ጠባይ ግምገማ መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

የኤጄንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ እንደገለፁት በመጪው በጋ የዝናብ ስርጭት መደበኛና ከመደበኛ በታች ነው።

የበጋ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የደቡብና ደቡብ ምስራቅ እንዲሁም ምስራቁ የሀገሪቷ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በታች የዝናብ ስርጭት እንደሚኖራቸው ትንበያው ያሳያል ብለዋል።

በተለይ የተወሰኑ የደቡብ ክልል አካባቢዎች፣ ቦረና፣ ጉጂ፣ ምስራቅ ባሌና ባሌ ዞን እንዲሁም በሶማሌ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የመጪው በጋ ዝናብ ስርጭት ከሚጠበቀው በታች እንደሚሆን ይጠበቃል ብለዋል።

በዚህም ሁሉም የባለድርሻ አካላት ሊኖር የሚችለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ የቅድመ ዝግጅትና መከላከል ስራ ላይ መረባረብ አለበት ብለዋል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጥኖ የሚደርሱ የሰብል ዝሪያዎች፣ የእንስሳት መኖና ድርቅን መቋቋም የሚችሉ ምርጥ ዘር ማዘጋጀትና ፈጥኖ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በግጦሽና በውሃ አቅርቦት ላይ ተገቢው ዝግጅትና ጥንቃቄ ካልተደረገ ተፅዕኖ የሚያሳድር የአየር ጠባይ መሆኑንም አመልክተው የክረምት ዝናብ ስርጭት መደበኛና ከመደበኛ በላይ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በደቡብና ደቡብ ምዕራብ የክረምት ዝናብ ቀደም ብሎ መጀመሩን ጠቅሰው ሰሜን ምስራቅና ማዕከላዊ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ መዘግየቱን የገለጹት አቶ ፈጠነ ሆኖም ከሰኔ ወር አጋማሽ ጀምሮ በሐምሌና ነሀሴ ወር የዝናብ ስርጭት ከመደበኛ በላይ መሆኑን ገልጸዋል።

የአሁኑ የዝናብ ስርጭት እስከ ጥቅምት ወር ድረስ የሚዘልቅ በመሆኑ በበጋ ወቅት ቆላማ የሀገሪቷ አካባቢዎች ላይ የከፋ ችግር እንዳይኖር ውሃን መያዝ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የሀገሪቷን ሁለንተናዊ ልማትና ዕድገት ማስቀጠል የሚቻለው በጥራት፣ በይዘትና በመጠን አስተማማኝ ትንበያ መስጠትና አገልግሎት ላይ ማዋል ሲቻል ነው ያሉት ደግሞ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚነስትር ዴኤታ ዶክተር አበረሃ አዱኛ ናቸው።

ተጠቃሚው ህብረተሰብ በኤጀንሲው የሚሰጡ የሜትዮሮሎጂ አገልግሎቶችን በትክክል ተገንዝቦ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በተለይም ድርቅ፣ ጎርፍና ተያያዥ የአየር ፀባይ የቅድመ ትንበያ፣ ማስጠንቀቂያና የምክክር አገልግሎቶች በሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም አመልክተዋል።

ለግብርና፣ ለአደጋ መከላከልና ዝግጅት፣ ለውሃ ዘርፍ፣ ለኢንዱስትሪ ልማትና አቪዬሽን ኢንዱስትሪ፣ ለቱሪዝምና ጤና የቅድመ ማስጠንቀቂያና በምክር አገልግሎት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ከኤጄንሲው ይጠበቃል ብለዋል።

በመጀመሪዎቹ የክረምት መግቢያ ግንቦትና ሰኔ ወር ላይ የዝናብ መዘገየት ቢኖርም በሐምሌና ነሀሴ ወር የክረምት ስርጭት ከአምናው በ40 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያሳያል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም