ሶስተኛው ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ በዋሽንግተን ዲሲ በመጭው ጥቅምት ይካሄዳል

84

መስከረም 14/2014 (ኢዜአ) ሶስተኛው ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ በዋሽንግተን ዲሲ በመጭው ጥቅምት ይካሄዳል።

አዘጋጆቹ ለኢዜአ በላኩት መግለጫ የሶስተኛው ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ በዲሲ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በመጭው ጥቅምት 16 ቀን 2021 (በኢትዮጵያ አቆጣጠር ጥቅምት 6 ቀን 2014 ዓ.ም.) በዋሽንግተን ዲሲ ይካሄዳል።

አጅናዋን ትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ ከ20 በላይ ኦሎምፒያኖች እና የዓለም ሻምፒዮኖች በዚህ ታላቅ ውድድር ላይ በክብር እንግዳነት ይሳተፋሉ። 

አርቲስት መሰረት መብራቴን የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ላደረገው ለኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማእከልም ድጋፍ ይደረጋል።

‘አብሮነት መሻል ነው’ በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው ይህ ዝግጅት ኢትዮጵያዊያንን ለማሰባሰብ፣ የመጀመሪያው ትውልድ ልጆችን ከባህላቸው ጋር የበለጠ ለማቀራረብ፣ እና ለተለያዩ በጎ ስራዎች ገቢ ለማሰባሰብ ዓላማው አድርጎ የሚከናወን ነው።

በዚህ ዝግጅት በሺወች የሚቆጠሩ የዲያስፖራው ማህበረሰብ አባላት የሚሳተፉ ሲሆን ለዚሁ የ5 ኪ.ሜ የቤተሰብ ሩጫ የውድድሩ ምዝገባ በአዘጋጆቹ ዌብሳይት በኦንላየን ላይ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ባለፉት ሁለት ዝግጅቶች ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኔሳ በቀለ፣ የዲባባ ቤተሰብ፣ ሚሊዮን ወልዴ፣ ፋጡማ ሮባ እና ሌሎችም በክብር እንግድነት መገኘታቸውን መግለጫው አስታውሷል።

የታላቅ የአፍሪካ ሩጫ በዲሲ ዋና አዘጋጅ ዶክተር ጋሻው አብዛ ፤ ዝግጅቱ ከአንድ ቀን የ5 ኪ.ሜ የቤተሰብ ሩጫ የበለጠ ኢትዮጵያዊያንን ይበልጥ የሚያቀራርብ ነው ብለዋል።

ከሩጫው ጎን ለጎን ለሚኖሩበት የአሜሪካ ማህበረሰብና ለትውልድ አገራችው ኢትዮጵያዊያ የጎላ አስተዋፅኦ ላደረጉ የዲያስፖራ ወገኖቻችን ሽልማት የሚሰጥበት መድረክ እንደሆነም አብራርተዋል።

የሩጫ ውድድርን እንደ መድረክ በመጠቀሞ በውጭ የሚኖሩ ወገኖቻችንን ግንኙነት ማጠናከር እና የባህል ልውውጥ ማድረግ ያስፈልጋል ብላለች የክብር እንግዳዋ ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ።

ዝግጅቱ ማህበረሰባችን የተለየ ቦታ የሚሰጠውን የአትሌቲክስ ስፖርት በመጠቀም አብሮነትን ማጎልበት የሚያስችል መሆኑንም ገልፃለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም