በትግራይ ክልል ምእራባዊ ዞን ከ284 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰሊጥ ሰብል ተሸፍኖ እየለማ ነው

51
ሁመራ ነሓሴ 9/2010 በትግራይ ክልል ምእራባዊ ዞን በዘንድሮው የመኸር እርሻ ከ284 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰሊጥ ሰብል ተሸፍኖ እየለማ መሆኑን የዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የጽህፈት ቤቱ አስባባሪ አቶ ተስፋይ የእብዮ ለኢዜአ እንደገለጹት በሰሊጥ ሰብል ከተሸፈነው መሬት ከ7 ሺህ ሄክታር በላዩ በመስመር የተዘራ ነው፡፡ በዘንድሮው የመኸር ወቅት በመስመር መዝራትን ጨምሮ የተለያየ የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እየለማ ካለው መሬት 700 ሺህ ኩንታል የሰሊጥ ምርት ለማግኘት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡ በምርት ዘመኑ ለማግኘት የታቀደው ምርት መጠን ባለፈው ዓመት ከተገኘው በ49 ሺህ ኩንታል ጭማሪ እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡ በቃፍታ ሑመራ ወረዳ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ አቶ ዮሀንስ ግርማይ በሰጡት አስተያየት 250 ሄክታር መሬት የሰሊጥ ምርጥ ዘርን በመጠቀም በመስመር መዝራታቸውን ተናግረዋል፡፡ የምርት ማሳደጊያ ግብአትን ተጠቅመው በመስመር መዝራታቸው ከአሁን በፊት በዘልማድ ከሚያለሙት አንድ ሄክታር መሬት ያገኙት የነበረውን ከሶስት ኩንታል ያልበለጠ ምርት ወደ አምስት ኩንታል ከፍ እንደሚል ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ቴክኖሎጂ ባለመጠቀማቸው ከአንድ ሄክታር መሬት ከሶስት ኩንታል ያልበለጠ ምርት ማግኘታቸውን የገለፁት ደግሞ አርሶ አደር አበበ ባየህ ናቸው፡፡ ዘንድሮ 50 ሄክታር መሬት ምርጥ ዘር በመጠቀምና በመስመር በመዝራታቸው ከአንድ ሄክታር መሬት እስከ ሰባት ኩንታል የሰሊጥ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡ በተጠናቀቀው የበጀት አመት በሰሜን ምእራብና ምእራበዊ ዞኖች ከተመረተው የሰሊጥ ምርት 743 ሺህ ኩንታሉን ወደ ውጭ በመላክ ከ98 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ መገኘቱን ከክልሉ ግብርና ምርቶች ፕሮሞሽን ኤጀንሲ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም