በጅማ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የፈጠራ ውጤቶችን ለማበልጸግ የተከፈተው ማዕከል ስራ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የፈጠራ ውጤቶችን ለማበልጸግ የተከፈተው ማዕከል ስራ ጀመረ
ጅማ፣ መስከረም 13/2014 (ኢዜአ) በጅማ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምርና የፈጠራ ውጤቶች ማበልፀጊያ ማእከል ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ጀማል አባፊጣ ገለፁ።
ማበልጸጊያ ማዕከሉ የሙከራ፣ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ማሳያ፣ የመወያያ ክፍልና ሌሎችም አገልግሎት መስጫዎች እንዳሉት ተገልጿል፡፡
የማእከሉ መከፈት ለፈጠራና ለቴክኖሎጂ ያለው አስተዋጽዎ የጎላ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ የሀገራችን የፋይናንስ ተቋማትም የፈጠራ ሀሳቦችን በማበረታታት ላይ መዋእለ ንዋያቸውን ቢያፈሱ በዘርፉ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል ጠቁመዋል።
በማበልጸጊያ ማእከሉ ከቡና፣ እንዶድ፣ አደይ አበባ፣ ጥቁር አዝሙድ፣ ሞሪንጋና መሰል እፅዋት የተቀመሙ ሳሙናዎች፣ ክሬሞች እና ስክራፖች ለዕይታ ቀርበዋል።
የኢትዮጵያ ስነ-ምህዳር ውጤቶች ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ምፅላል ክፍለየሱስ ዲጂታል ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ የተለያዩ የዕፅዋት ውጤቶችን ወደ አለም ገበያ ሊቀላቀሉ ስለሚችሉበት መንገድ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
እንደ ወይዘሮ ምጽላል ገለጻ አርሶ አደሩ በባህላዊ መንገድ አምርቶ ለአለም ገበያ ማቅረብ ስለማይችል ዩኒቨርሲቲዎች የእፅዋት ምርትን አበልጽገው አለምአቀፍ ተወዳዳሪ ምርት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
የቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ ማዕከላት መስፋፋት ተማሪዎች ያላቸውን ሀሳብ ወደ ተግባር ለመቀየር ያስችላቸዋል ተብሏል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም ዋቅጅራ እንዳብራሩት በዩኒቨርሲቲው ሶስት የስነ-ምህዳርና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ማበልፀጊያ ማዕከላት መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል።
ማዕከላቱ ለፈጠራ ስራዎች ምቹ ሁኔታን በማዘጋጀት አዳዲስ ሀሳብ ያላቸው ተማሪዎችና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ሊጠቀሙባቸው እንደሚችሉም ተናግረዋል።