ኢትዮጵያንና የመረጠንን ሕዝብ በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ ነን

113

አዲስ አበባ፤ መስከረም 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያንና የመረጣቸውን ሕዝብ በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ መልኩ የተለያዩ ድምጾች የሚሰሙበት እንደሚሆንም ነው የተገለጸው።

በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳድረው ያሸነፉ የፓርላማ አባላት የስራ ትውውቅ ስልጠና ወስደዋል።

በስልጠናው ከሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳድረው ያሸነፉ ተመራጮች ተሳትፈዋል።

ስልጠናው በዋናነት የሕዝብ ተወካዮች ሚና፣ የአባላት ስነ ምግባር ደንብ እና በምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

የስልጠናው ዓላማ የምክር ቤቱ አባላት ስራዎቻቸውን ያለምንም የመረጃ እጥረት እንዲያከናውኑ ማገዝ እንደሆነም ተጠቁሟል።

አዲሶቹ የምክር ቤቱ አባላት 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ከቀደሙት ምርጫዎች በተለየ መልኩ ነጻ፣ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ  እንደነበር አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያዊያን በነቂስ ወጥተው ድምጻቸውን በነጻነት ሰጥተዋል፤ ይህም አገራቸው ወደተሻለ የዴሞክራሲ ምዕራፍ እንድትሸጋገር ያላቸውን ጽኑ አቋም ያሳያል ነው ያሉት።

የፓርላማ አባላቱ ሕዝቡ የሚያነሳቸው የመልካም አስተዳደር፣ የልማትና የተጠቃሚነት ጥያቄዎች ለመመለስ ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።

ሙስና እና የሕዝብ ሃብት ምዝበራን እንደሚታገሉም እንዲሁ።

በዕለት ተዕለት የስራ እንቅስቃሴያቸው የመረጣቸው ሕዝብ የሰጣቸውን አደራ እንደማይዘነጉም ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው ከለውጡ በፊት በነበረው የምክር ቤቱ አሰራር አባላቱ በሚያነሱት ሃሳብ ይገመገሙ እንደነበር አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ በምክር ቤቱ አሰራር የተሻለ ነጻነት እንዲኖር ማስቻሉን ጠቅሰው፤ አባላቱም የፈለጉትን ሃሳብ የማንሳት ነጻነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሻለ ነጻነት ኖሮት ለሕዝብና ለአገር የሚጠቅም የትኛውም አይነት ሃሳብ የሚነሳበት እንደሚሆን ያላቸውን እምነትም ገልፀዋል።

አባላቱ ሃሳባቸውን የምክር ቤቱን ደንብ ባከበረና በተደራጀ መልኩ በማቅረብ የተሻለው እየተመረጠ አገር እንድትሻገር እንደሚሰራም ነው የጠቆሙት።

ምክር ቤቱ ባለፉት ሶስት ዓመታት የተጀመሩ መልካም ስራዎችን በማስቀጠል ኢትዮጵያን በተሻለ መልኩ እንደሚያገለግልም አውስተዋል።

ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው አገራዊ ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ሕዝቡ የሌሊት ቁርና ዝናብ ሳይበግረው በነቂስ በመውጣት ድምጹን ለመረጠው ፓርቲ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው ውጤትም የብልጽግና ፓርቲ መንግስት መመስረት የሚያስችለውን አብላጫ ድምጽ አግኝቷል።

በዚሁ መሰረት አዲሱ መንግስት መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም ይመሰረታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም