መጪዎቹን የአደባባይ በዓላት የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶችን በመተግበር ማክበር ይገባል

166

አዲስ አበባ፤ መስከረም 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኅብረተሰቡ መጪዎቹን የመስቀል ደመራና በቀጣይ የሚከበሩ በዓላት ላይ የኮቪድ መከላከያ መንገዶችን በትኩረት ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስገነዘበ።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ወቅታዊ የኮቪድ 19 ስርጭትን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

መድረኩ በኢትዮጵያ ያለው ወቅታዊ የኮቪድ 19 ስርጭት መረጃ እና መከላከያ መንገዶችን አተገባበር ያለበት ሁኔታ ለማሳወቅ ያለመ ነው ።

በተለይም በኮቪድ 19 ዙርያ የተሰበሰቡ መረጃዎች እና ቫይረሱን ለመከላከል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች  ለባለድርሻ አካላት በማቅረብ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ የተዘጋጀ ነው።

መረጃው የኮቪድ 19 ስርጭት በዕድሜ፣ በፆታ፣ በገጠር፣ በከተማ እንዲሁም በተለያዩ ክልሎች ያለበት ደረጃ ምን ይመስላል የሚለውን የዳሰሰ እንደሆነ እና ከ12 ሺህ በላይ አባወራዎች የተሳተፉበት መሆኑ ታውቋል።

በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፅጌረዳ ክፍሌ እንደገለጹት፤ እንደ ሀገር የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭት ከፍተኛ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። በከተሞች ያለው የቫይረሱ ስርጭት ከገጠር አኳያም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።

በተለይም በከተሞች ያለው የሻይረሱ መስፋፋት ከፍተኛ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፤ “በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው የመከላከያ እርምጃዎች አተገባበር ዝቅተኛ ነው” ብለዋል።

ህብረተሰቡ ቀጣይ የሚከበሩ ሃይማኖታዊ እና ህዝባዊ በዓላትን በሚያከብርበት ወቅት የኮቪድ 19 መከላከያ መንገዶች በመተግበር ማክበር አለበት።

መድረኮችን የሚያስተባብሩ አካላት  የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከላከያ መንገዶች ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸውም ዳይሬክተሯ ያስገነዘቡት።

በመድረኩ የኮቪድ 19 ወቅታዊ መረጃ ያቀረቡት ዶክተር ሚኪያስ ተፈሪ በኢትዮጵያ አዲሱ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭት እየተስፋፋ መምጣቱን ተናግረው፤ “በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ይገኛል ነው” ያሉት።

በየቀኑ በቫይረሱ ህይወታቸውን የሚያጡ እና በፅኑ የሚታመሙ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ያለው የቫይረሱ ስርጭት እና በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ መሆኑ አመልክተው፤ “ማህበረሰቡ ቫይረሱን ለመከላከል የተቀመጡ መመሪያዎችን ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባል” ነው ያሉት።

በቀጣይ በዓላት በሚከበሩበት ወቅት እና የተለያዩ መሰባሰቦች ሲደረጉ የአፍና አፍንጫ ጭንብል መልበስ፣ ርቀትን መጠበቅ እና የእጅ ንፅህና መጠበቅ እንዲሁም መከተብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አዲሱ የኮቪድ 19 ቫይረስ ዝርያ (ዴልታ) በሀገራችን በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስቴር መግለፁ ይታወሳል።