የክልሉን ሰላምና ፀጥታ ለማስከበር ያልተቋረጠ ኦፕሬሽን እየተደረገ ነው - የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን

108

መስከረም 13/2013(ኢዜአ) ሀገሪቱን ለማዳን እየተካሄደ ያለውን የህልውና ዘመቻውን ከማገዙ በተጓዳኝ የክልሉን ሰላምና ፀጥታ ለማስከበር ያልተቋረጠ ኦፕሬሽን በመድረግ ላይ መሆኑን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ከሰሞኑ ሰላማዊ ትግሉን ለመቀላቀል ወደ ሀገር ቤት ከተመለሰው ጎልቻ ዴንጌ አርአያ ተከትለው ሌሎች በተሳሳተ መንገድ  የሚንቀሳቀሱ የሸኔ አባላት ለመንግስት እጃቸውን እንዲሰጡም ኮሚሽኑ ጥሪ አስተላልፏል።

የክልሉ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነርና  የኮሙኒኬሽን ዘርፍ ሃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ጌታቸው ኢትቻ በተለይም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ተላላኪው ሸኔ በክልሉ የተወሰኑ አካባቢዎች በጥፋት ተግባሩ የቀጠለ ቢሆንም ከክልሉ የጸጥታ ዘርፍ አቅም በላይ የሆነ የጠላት እንቅስቃሴ የለም።

አሸባሪው ህወሃትም ሆነ ተላላኪው ሸኔ ትልቁ መሳሪያቸው የውሸት ፕሮፖጋንዳ መሆኑን ያወሱት ረዳት ኮሚሽነሩ፤  ህብረተሰቡ ይህንን አውቆ በተለይም በማህበራዊ የትስስር ገፆች በሚነዛ የውሸት ወሬ መደናገር እንደሌለበትም ነው ያስታወቁት።

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ከተከፈተብን ጦርነት በተጨማሪ በክልሉ የተወሰኑ አካባቢዎች የተላላኪው ሸኔ እንቅስቃሴ አለ ያሉት ረዳት ኮሚሽነር ጌታቸው፤ ይሁንና መንገድ መዝጋት፣ ፎቶ መነሳትና ያልማረከውን ማረኩ ብሎ ከመሸሽና ከመመታት ውጭ የሚያሰጋ ደረጃ ላይ እንደሌለ ነው የተናገሩት።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ከፌዴራል እና አካባቢ የፀጥታ አካላት ጋር የተቀናጀና ለአፍታም ያልተቋረጠ ጠላትን የመደምሰስ ኦፕሬሽን ላይ መሆኑን ህብረተሰቡ ሊገነዘብ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ብዙዎቹ የሸኔ ታጣቂዎች ከጥፋት መንገዳቸው በመመለስ ላይ መሆናቸውን የገለጹት ረዳት ኮሚሽነሩ፤  የቀሩት ታጣቂዎችም ከሰሞኑ ወደ ሰላሙ ከተመለሰው የደቡብ ኦሮሚያ የሸኔ መሪ የነበረው ጎልቻ ዴንጌን አርአያ ተከትለው ሌሎችም  አባላት ለመንግስት እጃቸውን እንዲሰጡ ከሚሽኑ ጥሪ አቅርበዋል።

በመጨረሻም ረዳት ኮሚሽነር ጌታቸው ኢትቻ፤ ለክልሉና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መልካም የመስቀልና የኢሬቻ በዓል እንዲሆን በኮሚሽኑ ስም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም