ምርምሮች የሚፈለገውን ለውጥ እንዲያመጡ የሥነ ምግባር ምሰሶዎች በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል

1142

ሐረማያ፤ መስከረም 13/2014(ኢዜአ) ምርምሮች የሀገሪቱን ችግሮች በመፍታት ለውጥ እንዲያመጡ የሥነ ምግባር መሠረታዊ ምሰሶዎች በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል እንደሚያስፈልግ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተባብራቸው አምስት መንግሥታዊ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ተቋማት የተሳተፉበት በምርምር ሥነ ምግባር ላይ ያተኮረ ስልጠና ዛሬ በዩኒቨርሲቲው ተጀምሯል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ስልጠና ሲጀመር ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት እንዳስገነዘቡት፤ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ነባር ተመራማሪዎች ወጣት ተመራማሪዎችን በየሙያ ዘርፉ ዓይነትና ብዛት ማፍራት ይጠበቅባቸዋል።


ምርምሮችና ጥናቶች የሀገሪቱን ችግሮች በመፍታት የሚፈለገውን ለውጥ እንዲያመጡ የሥነ ምግባር መሠረታዊ ምሰሶዎች በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በዚህም በሰው፣እንሰሳትና አካባቢ ላይ ተፅዕኖ ሳይፈጥሩ መፍትሄ እንደሚያስገኙ ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል።

በቀጣይ መሰል የአቅም ግንባታን በማጠናከር ጥራታቸውን የጠበቁ ምርምሮችና ጥናቶችን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መንግሥቱ ኡርጌ፤ ምርምሮችና ጥናቶች የሚፈለገውን ለውጥ እንዲያመጡ በሥነ ምግባር፣በዕውቀትና በኃላፊነት መከናወን እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ለምርምር የጀርባ አጥንት የሆነው “የምርምር ሥነ ምግባር መሠረታዊያን “ወጥ በሆነ መንገድ ተዘጋጅቶ በዩኒቨርሲቲዎች መተግበር እንዳለበትም ተናግረዋል።

በስልጠናው የቀብሪ ደሃር፣ድሬዳዋ ፣ኦዳቡልቱም፣ጅግጅጋ፣ሰመራ እና በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ የግል ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም የምስራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች የግብርናና የጤና ተቋማት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

ስልጠናው በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲሰጥ ለአምስተኛ፣በዩኒቨርሲቲው ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ መዘጋጀቱ በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ ተመልክቷል።