የአሸባሪው ቡድን ጭፍጨፋ በራያ ቆቦ

142

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራ ክልል ራያ ቆቦ ከተማ እና የገጠር ቀበሌዎች በሚኖሩ ሲቪል ዜጎች ላይ ከባድ ጭፍጨፋ፣ ዘረፋና የከባድ መሳሪያ ድብደባ መፈጸሙን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

የዐይን እማኞችን ጠቅሶ ባሰፈረው ዘገባ አሸባሪው ቡድን በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ላይ ከቆቦ ከተማ በስተደቡብ 7 ኪሎሜትር ርቃ በምትገኘው ገደመዩ ቀበሌ በነዋሪዎች ላይ ዘረፋና ጭፍጨፋ መፈጸሙን አመልክቷል።

በጥቃቱም በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች መገደላቸውና መቁሳላቸውን ነው የዜና ምንጩ የዘገበው።

በወቅቱ የአሸባሪው ቡድን በቀበሌው የቤት ለቤት አሰሳ ለማካሄድ ያደረገው ሙከራ ከአካባቢው ማኅበረሰብ በገጠመው መከላከል ወደኋላ ለማፈግፈግ መገደዱን ያመለከተው ዘገባ ወደኋላ ሲሸሽ ግን ንጹሃን ዜጎችን በመግደልና በመዝረፍ ጉዳት ማድረሱን የዐይን እማኞችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

ቡድኑ ወደ ኋላ ሲሸሽ የፈጸመው ጭፍጨፋ አልበቃ ብሎት በቀጣዩ ቀን ሃይሉን አደራጅቶ ዳግም በመመለስ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የከፋ ጥቃት ፈጽሟል።

የዜና ምንጩ የአካባቢውን አርሶ አደሮችና ለእርሻ ሥራ ከአጎራባች ደጋማ አካባቢ የመጡ የግብርና ሰራተኞችን አሸባሪው ቡድን የጥቃቱ ሰለባ እንዳደረጋቸው ጭፍጨፋው ሲፈጸም በስፍራው የነበሩ የዐይን እማኞችን ጠቅሶ ዘግቧል።

በወቅቱ በአንድ የመኖሪያ ግቢ ውስጥ 7 ሰዎች ተገድለው ማየቱን የገለጸው የዐይን እማኝ ከሰባቱ አራቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት እንደነበሩ ተናግሯል። ከአካባቢው ሸሽቶ ወደ ደሴ ከተማ በሚሄድበት ጊዜ በየመንገዱ በርካታ የተገደሉ ሰዎች መመለከቱንም ገልጿል።

አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በደሴ ከተማ አግኝቶ ያነጋገረው ሌላው የዐይን እማኝ በበኩሉ በቆቦ አቅራቢያ የምትገኘውን የዞብል ቀበሌን ከጥቃቱ በኋላ ሄዶ ማየቱን ገልጾ በርካታ እስክሬንና በርካታ ህንፃዎች ወደ ፍርስራሽ ተቀይረው ማየቱን ተናግሯል።

አሸባሪ ቡድኑ በጅምላ በሚፈጽመው ጥቃት ንጹሃን ዜጎችና ንብረታቸውን ከማውደሙ ባለፈ የጤናን ጨምሮ መንግሥታዊ ተቋማት መዘረፋቸውና መውደማቸውን ነው የዐይን እማኙን ጠቅሶ ኤ.ኤፍ.ፒ የዘገበው።

አሸባሪው ቡድን ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች በንፁሐን ሰዎች ላይ ጭፍጨፋ መፈጸሙን በተደጋጋሚ ሲገለጽ መቆየቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በቅርቡ ባወጣው መግለጫ በቆቦ ከተማና በዙሪያው ባሉ የገጠር ከተሞች አሸባሪው ቡድን በሲቪሎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጸሙን አመልክቷል። በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ የቤት ለቤት አሰሳና ግድያ፣ ዝርፊያ እንዲሁም የሲቪል መሰረተ ልማቶች ላይ ውድመት ማድረሳቸውን ጠቅሶ ምርመራ እንደሚያደርግ ገልጿል።

"በየቤቱ ጦርነቱን ፈርቶ የተቀመጠውን ሰው ሁሉ ቤት ለቤት እየዞሩ ገደሉ። ከዚያ ውጪ በእርሻ ቦታዎች አረም ሲያርም ውሎ ወደ ቤቱ የሚገባውን ሰው ሁሉ መንገድ ላይ እየጠበቁ ገደሉት" በማለት ስለጉዳዩ ለቢቢሲ ያብራራው የአይን እማኝ ጭፍጨፋው እጅግ የከፋ እንደነበር ተናግሯል።

በተመሳሳይ ፍራንስ 24 የተሰኘው የፈረንሣይ ቴሌቪዥን ባለፈው ማክሰኞ ምሽት ባሰራጨው በፊልም የተደገፈ ዘገባ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በተለያዩ አማራ ክልል ነዋሪዎች ላይ አስከፊ ጭፍጨፋ መፈጸሙን ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም